ሰኞ ፣14 ኦክቶበር 2013

ጠቃሚ ምክር

                                                                                          በዲ/ን ቃለአብ ካሣዬ

የቅድስት አርሴማ ጦማር
                                                                                    ‹‹ድልም ብዙ ምክር ባለበት ዘንድ ነው››  ምሳ. 24÷6
ተመክሮ አይድን አትበለው!

ወዳጄ ሆይ፡-እነሆ ጎበዝ ትሆን ዘነድ ሰነፍ አትሁን፡፡ ስንፍና ያለምንም ህመም አልጋ ያስይዝሃል፤ ለነገሩ አልጋ ያስያዘህ ስንፍና ራሱ በሽታ ስለሆነ ነው፡፡ ደግሞም ሰነፍ አልጋም ቢለቅ ሥፍራውን ሁሉ አልጋ ያደርገዋል፡፡ ጥንታውያን ሰዎች ‹‹ሰነፍ ካልሠራ፤ የለውም ሥፍራ›  ይላሉ፡፡ ሆኖም ‹‹ሰነፍ የሚሠራበት ሥፍራ ባይኖረው የሚጣላበት ሥፍራ አያጣም››፤የሚለው ንግርት ይፈፀም ዘንድ ነው ብዬ ልሣቅ እንጂ፡፡ አንዳንድ ቀናተኞች ስንፍና ይወገድ ዘንድ  በሰነፍ ጀርባ ላይ  በትር ሲያሣርፉ ኖረዋል፤ በትር ግን በሰነፍ ጀርባ ላይ ቄጤማ ነው፤ አይመክረውምና!!! ሰነፍን ያስተኛው ልቡ እያለ የተኛበት ጀርባው የሚገረፈው ስለምንድር ነው እላለሁ?

      ወዳጄ ሆይ ፡- ሰነፍ ቢሰንፍም ሰነፍን ለመምከር ግን አትስነፍ ‹‹ ሰነፍ ደስ እንዲለው በማይገባው አመስግነው!!! ከሚለው ብሂል ጋር እንዳትስማማ እለምንሃለሁ፤ ይልቁንም የሚገባውን ውቀሰው!!! ‹‹ ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም›› ይላልና አንተንም አታስፈልገኝም ቢልህ አትዘንበት (መዝ .13÷1):: ተመክሮ አይድን ነህ !አትበለው፤‹‹ ከሰነፍ ዝምድና፤ እጅ እግር የሌለው መልካም ቀን ይሻላል፤ ለሠው ጥግ ይሰጣልና›› ቢባልም  አንተ ግን ክርስቲያን ነህና ወዳጅነትህን አታቋርጥበት! አንተ ዘመድ ሁነውና የብርታት ጥግ ስጠው፡፡ ከሰነፍ ዘንድ ስንፍናን አትማር፤ እርሱ ግን ከአንተ ጉብዝናን ይማር ዘንድ በርታ፡፡ በረከትህ ይድረሰው እንጂ ርግማኑ አይድረስህ፡፡
ከሰነፍ አፍ የሐኬት እንጀራ እና ምክንያት አይጠፉምና ታገሠው፤ ሰነፍ የቆረሰውን እንጀራ አፉጋ እስኪያደርሰው ሲሠለቸውም ልታይ ትችላለህና ‹‹ ይህስ አይለወጥም!››አትበለው፤ አንተ ድከምለት እንጂ የሚለውጠው ሌላ ነው!!! ለሰነፍ የሚያዝን ሰው አስተዋይ ነው፤ የሰነፍንም እናት ከሀዘን ይታደጋታል፡፡ የመንታ እናት ተንጋላ ትሞታለች፤ የሰነፍን እናት ግን ሀዘን በቁሟ ይገድላታና፡፡ ( ምሳ. 7÷21 እና 25)፡፡ ሰነፍ ብትመክረው ወይ ይቆጣል አልያ ይስቃል፡፡ አንተ ግን ሳቁም ቁጣውም አይገድልህምና በቻልከው መጠን እርዳው፡፡ ወዳጄ እውነት እልሃለሁ ፤ሰነፍን ከመምከር ብዛት ትን ቢልህ ውሃ ጠጣ እንጂ ተስፋ አትቁረጥ! እግዚአብሔር የእኛ የሰው ልጆችን ደስታ የደበቀው ሠርተን በመድከማች ውስጥ እንደሆነ ሳትታክት ንገረው !ላባችን ውስጥ ፣ ጥረታችን ውስጥ ዕረፍት እንዳለ በትግዕስት ዘክረው! ጠቢቡ ሰለሞንም፡- ‹‹ሰው በሥራው ደስ ከሚለው በቀር ሌላ መልካም  ነገር እንደሌለ አየሁ፤ ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ያይ ዘንድ የሚመጣው ማን ነው?›› ብሎ እንደነገረን  ዘንድ ነው ( መክ .3÷22)፡፡ አዎ ወዳጄ፡- ሳይደክመው የሚያርፍ ሰነፍ ነውና ሰነፍን አበርታልኝ ፡፡የሰነፍ ግፍ ለገብስም ተርፎ ገብስም ሰነፍ ተባለ፤ ሰነፍ ገብስ ሲወቀጥ ገለባው ቶሎ ይለቀዋል፤ ሰነፍን ብትወቅጠው ግን ቶሎ ከስንፍናው አይገላገልምና ጽና፡፡
      ‹‹ ሰነፍን በሙቀጫ ውስጥ ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠው ስንፍናው በእርሱ አይርቅም››(ምሳ. 27÷22)፡፡ ከሰነፍ ሰው ሰነፍ ገብስ እንዴት ተሻለ?ብለህ እንዳትጠይቀኝ !አንዳንዴ እንዲህም ይሆናል፡፡
ነጮቹ ስንፍናን “the idea of doing nothing when things need doing” ይላሉ ደግሞም ‹‹Sign of weakness or shirking” ብለው ያክሉበታል፡፡
      አንዳንዴ ስንፍና ሊቋቋሙት የሚገባን ነገር መቋቋም መሰልቸት ነው፡፡ ስንፍና አለመቻል አይደለም፤ መቻልን አለመጠቀም ነው! የቀላልን ነገር ክብደት አምኖ መቀበል ነው! አሁን ማድረግ የሚቻለንን ‹‹አሁን አይቻለኝም ፤ነገ ነው የምችለው›› ማለት ነው፡፡ ሰነፍ- ነገም አሁን ሆኖ ሲመጣ ሌላ ነገን  ናፋቂ ነው፡፡ የአሁን ረሃብተኛ ፤የነገ ጥመኛ ሁለቱም ውስጥ ያልታደለ ነውና ሰነፍን በስንፍናው አውላላ ሜዳ ላይ አትለፈው፡፡ ብዙ የሥነ- ባህርይ አጥኚዎች ስንፍናን ለመርታት ተደጋጋሚ ፍቅር ተኮር ምክሮች ፣ ቅልጥፍናን የሚያነቃቁ ቀላል እንቅስቃሴዎችና፤ ተስፋን የሚፈነጥቁ ግልጽ የሕይወት ግቦችን ማስቀመጥ መልካም መሆኑን ያወሳሉ  እልሃለሁ፤ አንተም ወዳጄ ሆይ፡- ለሰነፍ ሰው የእውነት ወዳጅ ሁነው፤ አንተ ካልሆንህ ሌላ ማን ይሆነው ይሆን? እንኳን ሰነፍ ሰው ጎበዝም ሰው ወዳጅ ሲያጣ ይሞታልና፡፡የጥበብ ሰው አበባው መላኩ፡-

‹‹አባ ታጠቅ የቋራውም ፤
ስንቱን በግብሩ የሞገተ፤
አፍሎ ሥራይ ሳይበግረው፤
ለደብተራ ውግ ያቃተ፤፤
ለእንግሊዝ ክንዱን ሳያጥፍ፤
ስንቱን በሰይፉ እንዳልሸለተ፤
ተዋበች እንኳን፤
ስትሞት ችሎ፤
ገብርዬ ሲሞት ነው
የሞተ !!!››
     
      ብሎ የቀመመው ልቤን ይነካኛል፡፡ እናም ነው እኔ የምልህ፤ እናም ሰነፍ ጎበዝ እስኪሆን ድረስ ጐብዝ! የእግዚአብሔርም ፍቅር ከአንተ ጋር ጸንታ ትኖራለች!!! ‹‹ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው ፤ሰውን ሁሉ ታገሡ›› (2ኛ ተሰ .5÷14)፡፡

ሰኞ ፣26 ኦገስት 2013

የእሑድ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

የእሑድ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)፡-  በዚህ ዕለት እመቤታችን ከወትሮው ይልቅ ቀደም ብላ መጥታለች፡፡ “ዛቲ ዕለት ተዓቢ እምኩሎን ዕለታት፤ ወውዳሲያቲሃኒ የዓብያ እምኵሉ ውዳሴያት - ከዕለታት ኹሉ ይህቺ ዕለት ታላቅ ናት፤ ከውዳሲያቱም ኹሉ የዚች ዕለት ውዳሴ ታላቅ ነው” አለችውና ባረከችው፡፡ እርሱም በቤተ መቅደስ ባሉ ንዋያት ማለትም፡- በመሶበ ወርቅ፣ በተቅዋመ ወርቅ፣ በማዕጠንተ ወርቅ፣ በበትረ አሮን እየመሰለ ሲያመሰግናት አድሯል፡፡

 ፩. ንዕድ ክብርት ሆይ! ከሴቶች ተለይተሽ የሥላሴ ባለሟል ተባልሽ፡፡ ከተለዩ የተለየሽ፣ ከከበሩ የከበርሽ፣ ቅዱሳን ኪሩቤል የተሣሉብሽ፣ ቅዱሳን ካህናት የሚያመሰግኑሽ ኹለተኛ ክፍል አንቺ ነሽ /ዘጸ.፳፮፡፩-፴/፡፡
 ሕ የተጻፈባት ጽላት ያለብሽ የምትባዪ አንቺ ነሽ /ዘጸ.፴፪፡፲፭-፲፱/፡፡ ኪዳንም ያልኹት በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፉ (በግብር አምላካዊ የተገኙ) ዐሥሩ ቃላት ናቸው፡፡ ዐሥርቱ ቃላትን በጽላቱ ጽፎ እንዳኖረ ኹሉ ዋሕድ ቃለ እግዚአብሔርም በአፃብዐ መንፈስ ቅዱስ (ያለ ወንድ ዘር፣ በግብረ መንፈስ ቅዱስ) በማኅፀንሽ እንዲቀረጽ ኾኗልና የሙሴ ጽላት አንቺ ነሽ /ቅዳ.ማር. ቁ.፴፫/፡፡ ዐጤ ዘርዐ ያዕቆብም በነገረ ማርያም መጽሐፉ፡- “… ወማኅፀናሰ ለማርያም ድንግል በክልኤ ይትሜሰል በጽላት ዘተጽሕፈ ውስቴታ ዐሠርተ ቃላት፡፡ ወዐሠርተ ቃላት ቀዳሜ ስሙ ለወልዳ ውእቱ ዘውእቱ የውጣ ዘተሰምየ በኈልቄ ዐሠርተ ቃላት - … በኹለት ወገን ድንግል የምትኾን የማርያም ማኅፀንስ ዐሥሩ ቃላት በውስጧ በተጻፈ ጽላት ይመሰላል፡፡ ዐሥሩ ቃላትም የልጇ የኢየሱስ ክርስቶስ የመዠመርያ ስሙ ነው፤ ያውም የውጣ በዐሥሩ ቃላት የተጠራ ነው” ብሏል /ነገረ ማርያም በብሉይ ኪዳን፣ ክፍል ፩፣ ገጽ ፻፳፰፣ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ/፡፡   
 ከአንቺ ሳይለወጥ ሰው ኾነን፡፡ ለኦሪት ሳይኾን ለወንጌል ሊቀ ካህናት ኾነን፡፡ ለምድረ ርስት ሳይኾን ለመንግሥተ ሰማያት አስታራቂ ኾነን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን፤ እርሱም የበደላችን ስርየት ነው” እንዲል በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን አዳናቸው /ኤፌ.፩፡፯/፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የኤፌሶንን መልእት በተረጐመበት በአንደኛው ድርሳኑ ላይ፡- “ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኘነው ሥርየተ ኃጢአት በርግጥ ታላቅ ነው፡፡ ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው በልጁ ደም መኾኑ ግን ከምንም በላይ ታላቅ ነው” በማለት የእግዚአብሔር ከኅሊናት የሚያልፈውን የማዳን ምሥጢር (ፍቅር) በመደነቅ ተናግሯል፡፡
በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን ካዳነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
                                                            
፪. ኹል ጊዜ ንጽሕት የምትኾኚ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! ስለዚህ ነገርላችን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለንም፡፡ ሰውን ከሚወድ ሰው ከሚወደው ከርሱ ይቅርታን እናገኝ ዘንድ ኹል ጊዜ ዓይነ ልቦናችንን ወዳንቺ እንሰቅላለን፡፡
 ሸምሸር ሰጢን ከሚባል ከማይነቅዝ (በአምልኮተ ጣዖት ከማይለወጥ) እንጨት የተቀረጸ በአፍአ በውስጥ በወርቅ የተለበጠ ታቦት አካላዊ ቃልን ይመስልልናል /ዘጸ.፳፭፡፱-፳/፡፡ ይህ ንጹሕ የሚኾን፣ መለወጥ የሌለበት እርሱ ባለመለወጡ አለመለወጧን ነገራት፤ ከአብ ዕሪና ባለመለየቱም አለማለየቷን ነገራት (አምላክ ወሰብእ ኾኖ እርሷም እም ወድንግል መኾኗን ነገራት)፡፡ ከጥበብ በሚበልጥ ጥበብም ዘር ምክንያት ሳይኾነው እንደ እኛ ሰው ኾነ፡፡ አበው፡- “ዓለሙን ከፈጠረበት ጥበብ ይልቅ ሰው ኾኖ ዓለሙን ያዳነበት ጥበብ ይበልጣል” የሚሉትም ስለዚሁ ነው፡፡ አደፍ ጉድፍ ሳያገኝሽ መለኮቱን አዋሕዶ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ መለኮቱን አዋሕዶ ሰው ከኾነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡
፫.  እግዚአብሔር በፈጠራቸው በኪሩቤል አምሳል፤ ሙሴ የሣላቸው ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደሰ ሙሴ አንቺ ነሽ፡፡ አንድም እግዚአብሔር በፈጠራቸው በኪሩቤል አምሳል፣ ሰሎሞን የሣላቸው ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደሰ ሰሎሞን አንቺ ነሽ፡፡ ጌታ በማኅፀንሽ ያደረብሽ አማናዊቷ መቅደስ አንቺ ነሽ፡፡ ሳይለወጥ ካንቺ ሰው የኾነው አካላዊ ቃል በውስጥ በአፍአ በነፍስ በሥጋ ኃጢአታችንን የሚያስተሠርይልን ኾነ፡፡ ኃጢአታችንን ከሚያስተሠርይልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡

፬. መና ያለብሽ መሶበ ወርቅ አንቺ ነሽ /ዘጸ.፲፮፡፴፫-፴፬/፡፡ ይኸውም መና የተባለው ከሰማይ የወረደና ፱ ወር ከ፭ ቀን በማኅፀንሽ የተሸከምሽው ነው፡፡ እርሱም “አበዊክሙሰ መና በልዑ በገዳም ወሞቱ - አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ሞቱም” እንዳለው ያይደለ፤ ይልቁንም ለሰው ኹሉ ሕይወት የሚያድል ኅብስት ነው /ዮሐ.፮፡፶/፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በአንቀጸ ብርሃን ላይ፡- “አስተማሰልናኪ ቅድስት ወብፅዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት በመሶበ ወርቅ ዘውስቴታ ኅብስተ ሕይወት ዘወረደ እምሰማያት ወሃቤ ሕይወት ለኵሉ ዘየአምን ኪያሁ ወይበልዕ እምኔሁ በአሚን ወበልብ ሥሙር ምስለ እለ በየማኑ - የተለየሽና ደግ የኾንሽ የተመሰገንሽና የተባረክሽ የከበርሽና ከፍ ከፍ ያልሽ ሆይ! የሕይወት ኅብስት ባለበት በወርቅ መሶብ መሰልንሽ፡፡ የሕይወት ኅብስትም በቀኙ ካሉ ጻድቃን ጋር እርሱን ለሚያምን በሃይማኖትና ፈቃደኛ በኾነ ልብ ከእርሱ ለሚበላም ኹሉ ሕይወትን የሚሰጥ ከሰማይ የወረደ ነው” ብሏል /ቁ.፯/፡፡ ዳግመኛም አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫ፡- ኦ መሶብ ቤተ ልሔማዊት ዘወለደቶ ለኅብስተ ሰማይ ዘኢያብቌልዎ ዝናማት ወዘኢሐፀንዎ አየራት - ዝናማት ያላበቀሉትን አየራት ያላሳደጉትን የሰማዩን እንጀራ የወለድሽው ቤተ ልሔማዊት መሶብ ሆይ” በማለት መስክሯል /አርጋኖን ዘረቡዕ/፡፡ ከአባቶች አንዱም፡- “ድንግል ሆይ! በእውነቱ አንቺ ከታላላቅ ይልቅ ታላቅ ነሽ፡፡ ማኅደረ ቃለ አብ ሆይ! አንቺን ሊተካከል የሚችል ታላቅ ማን ነው? ድንግል ሆይ! ከየትኛው ፍጥረት ጋር አወዳድርሻለሁ? አንቺ ቀድሞ በወርቅ ካጌጠችው የሕጉ ታቦት ይልቅ በንጽሕና ያጌጥሽ ታላቅ ነሽ! እውነተኛውን መና የተሸከምሽ መሶበ ወርቅ አንቺ ነሽ፡፡ መና የተባለውም መለኮት የተዋሐደው ሥጋው ነው” ብሏል፡፡ ኅብስተ ሕይወት ከሚባል ልጅሽ ጸንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፭. ብርሃንነት ያለውን ፋና የተሸከምሽ የወርቅ ተቅዋም (መቅረዝ) አንቺ ነሽ /ዘጸ.፳፭፡፴፩-፵/፡፡ ይኸውም ፋና ለሰው ኹሉ ዕውቀትንሚገልጽ ብርሃን ነው፡፡ ጥንት ከሌለው ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው፡፡ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ሳይለወጥ ካንቺ ሰው የኾነው ነው፡፡ ሰውም በመኾኑም በድንቁርና በቀቢጸ ተስፋ ለምንኖር ለኛ አበራልን (ዕውቀትን ገልጸልን)፡፡ በጥበቡ ባደረገው ሥጋዌ እግረ ልቡናችንን ወደ ሕገ ወንጌል ጎዳና አቀናልን /ኢሳ.፱፡፩-፪፣ ማቴ.፬፡፲፬-፲፮/፡፡ ታላቁ የዜማ አባት ሊቁ ቅዱስ ያሬድም፡- “አንቲ ውእቱ ተቅዋም ዘወርቅ ዘኢገብራ እደ ኬንያ ዘሰብእ… - የብልሐተኛ እጅ ያልሠራት በውስጧም መብራት የሚያበሩባት የወርቅ መቅረዝ አንቺ ነሽ፤ ራሱ የአብ ብርሃን ያበራባታል እንጂ፡፡ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ወደ አንቺ መጥቶ አደረ፡፡ አምላክነቱም በዓለም ኹሉ አበራ፡፡ ጨለማን ከሰዎች ላይ አራቀ፡፡ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ በብርሃኔ እመኑ፤ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ ብሎ በሚያድን ቃሉ አዳነን” ብሏል /ቁ.፰፣ ዮሐ.፲፪፡፴፭፣ ፩ኛ ዮሐ.፩፡፭/፡፡ በጥበቡ ባደረገው ሥጋዌ እግረ ልቡናችንን ወደ ሕገ ወንጌል ጎዳና ከአቀናልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፮. ቡሩክ አሮን ከቤተ መቅደስ ይዞሽ የወጣ እሳትነት ያለውን ፍሕም የተሸከምሽ ማዕጠንተ ወርቅ አንቺ ነሽ /ዘጸ.፴፡፩-፰/፡፡ ፍሕም የተባለውም በአፍኣ በውስጥ በሥጋ በነፍስ ኃጢአትን የሚያስተሠርይ ነው፡፡ ይኸውም ከአንቺ ሰው የኾነውናወአንከረ አብ እምዝንቱ መሥዋዕት - ከዚህ መሥዋዕት የተነሣ አብ አደነቀ” እንዲል /ሃይ.አበ.፷፰፡፳፫/ ለአባቱ ራሱንማረ የተወደደ መሥዋዕት አድረጎ ያቀረበ አካላዊ ቃል ነው /ኤፌ.፭፡፪/፡፡ ራሱን ያማረ የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፯. አካላዊ ቃልን የወልድሽልን መልካም ርግብ ማርያም ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ከእሴይ ሥር የወጣሽ መዓዛ ሠናይ አበባ አንቺ ነሽ፡፡ መዐዛ ሰናይ የተባለውም የቅዱሳን መዐዛ የሚኾን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው /መጽሐፈ ድጓ፣ ገጽ.፻፺፱/፡፡ መዐዛ ሠናይ ከተባለ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፰. ሳይተክሏት የበቀለች፣ ውሃ ሳያጠጧትምለመለመች ያበበች ፲፪ በኵረ ሎሚ ያፈራች የአሮን በትር ነበረች /ዘኁ.፲፯፡፩-፲/፡፡ ከቤተ መቅደስ ፲፪ ዓመት ኑረሽ፣ ዘር ምክንያት ሳይኾነው ሰው ኾኖ ያዳነን እውነተኛ አምላካችንን ክርስቶስን የወለድሽልን አንቺም እንደርሷ ነሽ /ኢሳ.፯፡፲፬/፡፡ አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫም በአርጋኖን ዘሰኑይ ላይ፡- “ዕፀ ከርካዕ እንከ እሰምየኪ እስመ ከርካዕ ሠናየ ይጸጊ፤ ወሠናየ ይፈሪ፤ ወሠናየ ይጼኑ፤ ወከመ በትር ይቡስ ዘቦ ላዕሌሁ ወፅአ ዑፃዌ ክህነት አሥረጸ አዕጹቀ ወአቊጸለ ከርካዕ ምዑዘ፤ ወከማሁ አንቲኒ ነበርኪ ውስተ ቤተ መቅደስ ዐሠርተ ወክልኤተ ክራማተ ወፀነስኪዮ ለኢሱስ ዘእንበለ ዘርዐ ብእሲ - እንግዲህ የሎሚ ዕንጨት ብዬ እጠራሻለሁ፡፡ ሎሚ መልካሙን ያብባል፤ መልካሙን ፍሬ ያፈራል፡፡ በጐ በጐ ይሸታልና ዕጣ እንደ ወጣበት ደረቅ በትር ሳይተከል በቤተ መቅደስ ለምልሞ፣ ቅንጣት አውጥቶ፣ አብቦ ተገኘ፡፡ ሽታው ያማረ የተወደደውን ሎሚ አፈራ፡፡ እንዲሁም አንቺ በቤተ መቅደስ ዐሥራ ኹለት ዓመት ተቀምጠሸ ያለ ወንድ ዘር መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፀነስሺው” በማለት አብራርቶታል፡፡ ዳግመኛም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ፡- “ሳይተክሏትና ውሃ ሳያጠጧት የለመለመች የአሮን በትር በቤተ መቅደስ ነበረች፡፡ ለካህናት ዝግጁ ያደረጋት ነበረች፡፡ አንቺም በቅድስናና በንጽሕና ጸንተሸ እንደ እርሷ በቤተ መቅደስ ኖርሽ፡፡ ከቤተ መቅደስም በክብር በታላቅ ደስታ ወጣሽ፡፡ በእውነት የሕይወት ፍሬ የኾነ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከአንቺ ተገኘ፡፡ ቅድስት ሆይ! ከመልአኩ እንደተረዳሽው ከወንድ ያለመገናኘት ልጅን አገኘሽ፡፡ መልአኩ መንፈስ ቅዱስ መጥቶ ያድርብሻል፤ የልዑል ኀይልም ይጸልልሻል ብሎ ነግሮሽ ነበርና” በማለት አማናዊቷ የአሮን በትር እርሷ መኾኗን አስተምሯል /ቁ.፲፩/፡፡ ሰው ኾኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፱. ምልዕተ ክብር ሆይ! ከቅዱሳን ኹሉ ይልቅ ትለምኚልን ዘንድ ላንቺ ይጋባል፡፡ ከሊቃነ ጳጳሳት አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ ከመምህራን፣ ከሐዋርያትከ፸ አርድእትም አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ ከሱራፌልና ከኪሩቤል ይልቅ የሚበልጥ የመወደድ የመፈራት ግርማ አለሽ፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው፡- “ኦ ሙኃዘ ፍስሐ! ፈድፋደ ብኪ ግርማ ራዕይ ዘየዐቢ እም ኪሩቤል እለ ብዙኃት አዕይንቲሆሙ ወሱራፌል ፮ ክነፊሆሙ - የደስታ (የጌታ) መገኛ የምትኾኚ እምቤታችን ሆይ! ዐይናቸው ብዙ ከሚኾን ከኪሩቤል፣ ክንፋቸው ስድስት ከሚኾን ከሱራፌል ይልቅ በምእመናን ዘንድ የመወደድ፣ በአጋንንት በአይሁድ በመናፍቃን ዘንድ የመፈራት፣ በሥላሴ ዘንድም የባለሟልነት መልክ አለሽ” ይላል /ቁ.፳፪/፡፡ በእውነት የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ፡፡ ለሰውነታችን ሕይወትን የምታማልጅን አንቺ ነሽ፡፡ አንድነቱን ሦስተነቱን በማመን አጽንቶ ሥጋዌውን በማመን ያፀናን ዘንድ፣  “ጸጋሰ ሥርየተ ኃጢአት ይእቲ” እንዲል በቸርነቱ ብዛት ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ አማልጅን፡፡ ኃጢአታችንን ከሚያስተሠርይልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
ልመናዋ ክብሯ የልጅዋም ቸርነት ከኹላቸን ጋራ ለዘላለም ጸንቶ ይኑር አሜን፡፡
ልዩ ምስጋና
 ታናሽ ለምኾን ለእኔ የማይገባኝ ኾኖ ሳለ ስለ እመ አምላክ የውዳሴዋን ትርጓሜ እጽፍ ዘንድ ልቦናዬን ላነሣሣ ቸሩ መድኃኔ ዓለም ክብር ምስጋና ለእርሱ ይኹን፡፡ ውዳሴዋ ከበዛላቸው አበው በረከቷ እንድካፈል ለረዳችኝና በምልጃዋ ዘወትር የማትለየኝ እመ አምላክን አመሰግናለሁ፡፡ ዳግመኛም ይህ ሥራ የተቃና ይኾን ዘንድ ከመጀመርያ አንሥተው እስከ መጨረሻ ጽሑፉን ሳይሰለቹ ላረሙልኝ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እመ አምላክ ዋጋቸውን ትክፈልልኝ፡፡ አሜን!!!

††† ተፈጸመ †††

ድንግልማ በእውነት ተነሥታለች - በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ለተሐድሶዎች የተሰጠ ምላሽ

ድንግልማ በእውነት ተነሥታለች - በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ለተሐድሶዎች የተሰጠ ምላሽ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- እንኳን ለእመቤታችን በዓለ ዕርገት አደረሳችሁ፡፡
ዘሰ ይብል አፈቅረከኪ ወኢያፈቅር ተአምርኪ [ትንሣኤኪ ወዕርገትኪ] ክርስቲያናዊ፤
ኢክርስቱን ውእቱ አይሁዳዊ ወሠርፀ እስጢፋ ሐሳዊ፤
አንሰ እቤ በማኅሌተ ሰሎሞን ሰንቃዊ፤
አፈቅሮ ለፍግዕኪ ወለተ ይሁዳ ወሌዊ፤
ከመ መርዓቶ ያፈቅር ጽጌኪ መርዓዊ፡፡

እንደ ይሁዳ ስሙን የሚቃረን ግብር ሁልጊዜም የሚሠራውና ራሱን ‹‹ አባ ሰላማ ›› ብሎ የሚጠራው የተሐድሶዎች ብሎግ አንድ የሚያስደንቅ ጽሑፍ ሰሞኑን አስነብቦናል፡፡ የሚያስደንቅ ያልኩት ራሴን ባስደነቁኝ ሦስት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ለርእስነትና ሐሳቡን ለማስተላለፍ መሪ አድርጎ የተጠቀመው ጥቅስ መልእክቱ ከነገረ ጉዳዩ ያለውን ርቀትና አንድ ሰው ከካደ በኋላ ጥቅሶችን እስከምን ድረስ ሊያጣምም እንደሚችል ሳስብ አሁንም እደነቃለሁ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ክርስትና ከተመሠረተበትና በይፋ በብዙዎች ተቀባይነት እያገኘ ከመጣበት ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ብዙ የዓይን ምስክሮች አይተው ያስተላለፏቸውን ትውፊቶች ሁሉ ምን ያህል እንደሚጠሉ ሳስብ በዚያ ዘመን የነበሩ አይሁድ በአካለ ሥጋ የመመለስ እድል ገጥሟቸው ቢጠየቁ እንኳ  ‹‹ እንዴት ከእኛ በላይ ጠላችኋቸው›› ብለው የሚገረሙባቸው ስለሚመስለኝ እደነቃለሁ፡፡ ሦስተኛውና ሁልጊዜም ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ተሐድሶዎች የምደነቀው ደግሞ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብና ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ባላቸው ጥላቻ ነው ፡፡ አስተውሎ ለሚያይ ሰው ጽሑፍ ነክ ነገር ላይ ከተነሡ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን ወቅታዊ ነገር ላይ ከተነሡ ማኅበረ ቅዱሳንን አንዳንድ ጊዜ ሁለቱንም አንድ ላይ ካላመቼም የሚጽፉበትን ሰው ማኅበረ ቅዱሳን ወይም ዘርዐ ያዕቆብ ነክ አድርገው ካላቀረቡ መንፈሳቸው የሚቀጣቸው ይመስለኛል፡፡ ዓለም አቀፍና ልዩነት የሌለበት የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ነባር ትውፊቶች መካከል አንዱ የሆነውን የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት ለዘርዓ ያዕቆብ መስጠት ማለት ምን ያህል ድፍን ቅልነት ይሆን? እንዲህ የምለውና የምደነቀውም ብዙ ጊዜ የስሕተትና የክህደት ጽሑፍ ቢጽፉም እውነቱ የያዙትና በዚያም እንጸድቃለን ብለው የሚያስቡና ለዚያም ለመሰላቸው የሚተጉ ይመስለኝ ስለነበረ ነው፡፡ ይህን ጽሑፍ ሳየው ግን ‹‹ ኦርቶዶክስን እንዴት እናስጠላለን፤ ሰውንስ ከእምነት እንዴት እንለያለን?›› በሚል መንፈስ ብቻ እንደሚሠሩ ስለተረዳሁ ነው፡፡  አሁን አሁንማ እንደ መሸታ ቤት በየሥርቻው በከፈቷቸው ብሎጎቻቸው ዓይን ያወጣ ስድብና ምንም ዓይነት መሠረት የሌለው የስም ማጥፋት ቅርሻቶቻቸውን በመትፋት ላይ መሆናቸውን ሳይ አውሬው ብስጭቱ እየጨመረ የመጣው ወደፊት ሰማዕትነትን አይቶ እየፈራ ይመስላል ፡፡ 
በርግጥ ይህ ብሎግ በመኖሩ  ‹‹ ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው›› /ራእ 13 5/ ተብሎ የተነገረለት አውሬው ሥራውን እያበረታ መሆኑን እናያለን፡፡ በማያቋርጠው የሐሰትና የጠብ የስድብና የስም ማጥፋት እንዲሁም የኑፋቄና የክህደት ጽሑፎቻችሁም ‹‹ እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ ›› /ራእ 12 15/ የተባለውን አውሬው በገቢር የሚያሳይባችሁ የክሕደትና የኑፋቄ የአውሬው የትፋት ወንዞች መሆናችሁን ታረጋግጡልናላችሁ፡፡   ነገር ግን ‹‹ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው ›› /ራእ 12 16/ ተብሎ እንደተጻፈው ምድር ቤተ ክርስቲያን የእናንተን የክህደት መርዝ ታሰርገዋለች ፡፡ አሁንም እንደተለመደው ሁሉ ስሕተቶቻችሁን ከማሳየት እንጀምር፡፡
አውሬ ያበከተውን አትብሉ
 በመጽሐፍ ‹‹በእርሱም እንዳይረክስ፥ የሞተውን አውሬም የሰበረውን አይብላ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ›› /ዘሌ 22 8/ ተብሎ እንደተጻፈ አውሬ ያቆሰለው ደሙን መጥጦ ያበከተው የጫረው ሁሉ እንዳይበላ በኦሪቱ ታዝዟል፡፡ በላይኛው አንቀጽ ላይ ደግሞ አውሬው ማን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ነግሮናል፡፡ አንድ ሰው በጉ ወይም በሬው የእርሱ ቢሆንም  አውሬ ሊበላው ጭሮ ካቆሰለው ደሙን መጥጦ ከገደለው እንዳይበላው እንደተከለከለው ሁሉ ለሕይወታችን ምግብ በአምልኮታችንም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገን ከምናቀረበው ከመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አንዱን  ለይተው  ልክ አውሬ በጉን ከመንጋው ለይቶ እንደሚበላው  ወይም እንደሚያቆስለው አውሬ የተባለ መናፍቅም ወይም ከሐዲ ከእናቱ ወይም ከመንጋው ለይቶ በተሳሳተ ትርጉም ያቆሰለውን ወይም የጫረውን ወይም በክህደት አስተምህሮ የገደለውን መብላት ለእኛ የተከለከለ ነው፡፡ በኦሪቱ ትእዛዝ እንዳየነው በጉ ንብረትነቱ የሰው ቢሆንም አውሬ ስለነካው ብቻ እንደተከለከሉት ጥቅሱ የእኛውና ከእኛው መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ቢሆንም አውሬ መናፍቅ በጥርጥርና በክህደቱ መርዙ የወጋውን በልተን እንዳንጎዳ የተከለከለ ነው፡፡ ስለዚህም ጥቅስን እኛ ለነፍሳችን የምንመገበው በአውሬ መናፍቃን ትምህርት ያልተጫረና ያልረከሰ ሲሆን ብቻ መሆኑን ማስተዋል አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ መናፍቃን በተሳሳተ መንገድ ያጣመሙትን ሁሉ ለነፍሳችን ማቅረብ ራስን መቅጣት መሆኑን ማወቅና መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡
ለምሳሌ እመቤታችን አልተነሣችም አላረገችም ብሎ ለመካድ የግድ ጥቅስም የሚያስፈልገው አልነበረም፡፡ ‹‹ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም ››  / ዮሐ 3 13/ የሚለውን ጠቅሶ እጂግ በተዛባ መንገድ እመቤታችን አላረገችም ለማለት መጥቀስ ልክ በበጎቹ አውሬ እንደሚያደርገው የበጉን ደሙን ( የጥቅሱን ነፍሱን ምስጢሩን ወይም ዋና መልእክቱን ) መጥጦ ገድሎ አበክቶ መስጠት ነው፡፡ ቀጥታ በዚህ መንገድ እንተርጉመው ካልንማ መጀመሪያውኑ የሚለው ወደ ሰማይ የወጣው ከሰማይ የወረደው ከሆነ  ክርስቶስ ያረገው በተዋሐደው ሥጋ ነውና በውኑ ሥጋውን ከሰማይ ይዞ ወርዷልን? እንዲህማ ከሆነ የሰው ልጅ ተብሎስ እንዴት ሊጠራ ይችላል? እንዲህማ ከሆነ የራሱ ትምህርትና ንግግርም ሆነ ስለ እርሱ ሐዋርያትና ሊቃውንት ያስተማሩት ሁሉ ከንቱ ሆነ፡፡ ከሰማይ በውረድማ ከሆነ መላእክቱን እንኳ ብንተዋቸው ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ሦስተኛ ሰማይ የተነጠቀው ጥንቱን ከዚያ ቢመጣ ነውን? ወይስ ሔኖክና ኤልያስ ያረጉት ድሮውንም ከሰማይ የወረዱ በመሆናቸው ነው? ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ወርደው ያልተመለሱም አሉ፡፡ ለይስሐቅም ምትክ ሆኖ የተሰዋው ከሰማይ የወረደ ነበር፡፡ ለኤልያስም እንጎቻ በመሶብ ውኃም በማሠሮ ወርዶለት ነበረ፡፡ ጥቅሶችን የምትተረጉሙት እንደዚህ ከሆነ ‹‹ እኔ ስለ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክሬ እውነት አይደለም ›› / ዮሐ 5 31/ የሚለውንስ ምን ትሉለታላችሁ? በእውነት ጥቅስን እንዲህ ያለ ቦታውና ያለመልእክቱ መጠቀም በገዳመ ቆሮንቶስ ለጌታም ጥቅስ እየጠቀሰ ለመፈታተን ያላፈረውንና አሁንም ይህን ከማድረግ የማያፍረውን የማይሰለቸውንም ዲያብሎስን ያስመስላችሁ ወይም በእርሱ መንፈስ የምትሠሩ ፈታኞች መሆናችሁን ታረጋግጡ ካልሆነ በቀር የምትፈጥሩት ነገር የለም፡፡ ልክ ክፉ አውሬ በጉን ከመንጋው ለይቶ አድክሞ ይዞ ደሙን መጥጦ እንደሚገድለው ጥቅስንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ከመንጋውና ከመልእክቱ ለይቶ ምሥጢር ደሙን መጥጦ በማብከት ተሐድሶዎችን የሚተካከል ያለ አይመስለኝም፡፡
 ይህ ጥቅስ የተጠቀሰለት ዳግም የመወለድ ምስጢር ረቅቆበት አልገባው ላለው የአይሁድ መምህር ኒቆዲሞስ ነው፡፡ ከጥቅሱ ጌታችን ኒቆዲሞስን ከነበረበትም ዕውቀትና እምነት ከፍ እንዲልና ታላቁን ምሥጢረ ሃይማኖት እንዲረዳ እያደረገው እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ በፊቱ ቆሞ የሚያነጋግረው ጌታ ዕሩቅ ብእሲ ሳይሆን ከሰማይ አካላዊ ቃል መጥቶ በተዋሕዶተ ትስብእት የተገለጠ መሆኑንና በሚያየው ትስብእት ውስጥ የማያየው መለኮት ተዋሕዶ መኖሩን ትስብእትም ለዚህ የበቃው በተዋሕዶ እንጂ እንደ ቀደሙት ነቢያት በጸጋ አለመሆኑንና የባሕርይ አምላክ መሆኑን ነበር ያስረዳው፡፡ በርግጥም ወልደ እጓለመሕያው ጌታ ራሱን አምላክ ያደረገ ፍጡር አይደለም፡፡ አምላክነት ከጥንት ገንዘቡ ነው፤ ነገር ግን ይህን ሰማያዊነት፣ ቀዳማዊነትና፣ ፈጣሪነት፣ ሁሉን ማወቅና ከመወሰን ሳይወጡ መምላት፣ ከመግዘፍ ሳይወጡ መርቀቅ ( ቀድሞ በሰማይ የነበረውን) ትስብእት ወይ ሥጋ የወረሰው በተዋሕዶ ከቃል ነውና ‹‹ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም›› ሲል እውነተኛ ተዋሕዶውን አረጋገጠልን፡፡  ጥቅሱ ራሱ የሚፈጸመው  ‹‹ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው ›› በሚል ሐረግ ነው፡፡ ጌታ ራሱ በኒቆዲሞስ ፊት ሆኖ እያነጋገረው እያለ ራሱን ‹‹ በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው›› ሲል የጠቀሰው በዚያው ቅጽበት ወይም ቃል ሥጋን ከተዋሐደበት ቅጽበት ጀምሮ ሥጋ ቅድመ እርገትም በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ በክብር ያለና ፍጹም አምላክ መሆኑን ሲያስረዳው ነው፡፡ ምክንያቱም ከእርሱ ጋር ሲነጋገር ቢየየው በሰማይ የሌለ እንዳይመስለው ተዋሕዶውንና አምላክነቱን ለማስረዳት የተናገረው መሆኑን በዚህ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ እንደዚህማ ባይሆንና ጥቅሱ ለጌታ ለዕርገቱ የተነገረ ቢሆን ኖሮ ‹‹ አሁን በሰማይ የሚኖረው›› ለምን ይለዋል፡፡ ገና አላረገም ነበርና፡፡  ስለዚህ ጥቅሱ ከእመቤታችን ዕርገት ቀርቶ ከጌታም ዕርገት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ፡፡
ለመሆኑ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገትን ያስተማሩና የሰበኩ እነማን ናቸው? በግእዙ ያለው ታሪካችን ከሆነ ያስጠላችሁ እስኪ በሦስተኛ ክፍለ ዘመን ስለ እመቤታችን ድንቅ ድንቅ ስብከቶች የሰበከውን ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራትን ዘርዓ ያዕቆብ አስተማረህ ትሉታላችሁን? ወይስ  የእመቤታችን በዓለ ዕረፍቷ ከበዓለ ዕርገቷ ጋር በአንድ ላይ በጁሊያን አቆጣጠር ኦገስት 15 አንድ ላይ ይከበር ይል ለነበረው ለቁስጥንጥንያው ንጉሥ ለዮስጥንያኖስ ከጥንት ጀምሮ ከኢየሩሳሌም መጥቶ በመንበረ ማርቆስ ካቴድራል ቤተ መጻሕፍት ተቀምጦ የኖረውን የእመቤታችንን የዕረፍቷንና የዕርገቷን ዜና መጽሐፍ ተርጉሞ በመስጠት ዕረፍቷ ጥር 21 ዕርገቷ ነሐሴ 16 መሆኑን በመግለጽ ቢያንስ በዚያ ዘመን ሁለቱም በዓላት በየራሳቸው እንዲከበሩ እንጂ አንድ ላይ መከበሩ እንዳይታወጅ ያደረገው 33ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ የቴዎዶስዮስን (535 - 566) ሥራ ምን ልታደርጉት ነው? አትደብቁት በብዙ የዓለም ቋንቋዎች የተተረጎመ ነው፡፡ እንግዲህ እናስተውል ይህ ቴዎዶስዮስ በጽርእ (ግሪክ) ቋንቋ ተርጉሞ ለንጉሡ የሰጠው መጽሐፍ በዓሉ ከእርሱ ዘመን በፊት ተለያይቶ ይከበር እንደነበርና ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ያሉት የምስራቁ ክፍል አባቶች በዚህ ትውፊት ጸንተው ይጠቀሙበት እንደነበር አሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ምርምር ለሚያደርጉ ማስረጃ ሆኖ ያገልግላል፡፡ በቅርብ ጊዜ አሜሪካን ሀገር ያለው የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የነገረ መለኮት ከፍተኛ ትምህርት ቤት የሆነው የቅዱስ ቭላድሚር ሴሚናሪ ከሚያሳትማቸው እስከ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ አባቶች ስብከቶች (Patristic writings) መካከል አንዱ የእመቤታችንን ዕረፍትና ዕርገት (Dormition and Assumption) በተመለከተ በዚያ በጥንቱ ዘመን የተሰበኩ ስብከተ ሊቃውንትን አሰባስቦ የያዘ ነው፡፡ ይህ በዓል በጥንታውያኑ አበው ሲያከብሩት የመጣና እመቤታችን ዕረፍቷም ሆነ ዕርገቷ ከሐዋርያት ጀምሮ በኢየሩሳሌም ዙሪያ የነበሩ እጂግ ብዙ ደናግል ሴቶች በአካል በነበሩበት የተፈጸመ እንደሆነ ትውፊቱን የመዘገቡ መጻሕፍት ሁሉ የሚያረጋግጡት እውነታ ነው፡፡ በዚያ የነበሩ ሁሉ አይተው እንዳረጋገጡት ጌታ በሚያስደንቅ ግርማ የእመቤታችንን ነፍስ ሊቀበል በተገለጸ ጊዜ በአንድነት የሰገዱት ሐዋርያትና ደናግል ፍርሐት ርቆላቸው ቀና ሲሉ ሙሴ ከፊት ሆኖ ሌሎች ነቢያትና ጻድቃን ጌታን ከብበው ዳዊት በበገናው ‹‹ ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ፤ አንተ ወታቦተ መቅደስከ›› የሚለውን መዝሙሩን ሲዘምር ሁሉም በአንድነት አይተዋል፤ ሰምተዋል፡፡ ይህ የተረጋገጠ ታሪክ ነው፡፡ የነበሩት ሁሉ መስክረውታልና፡፡ እንግዲህ ሐዋርያትና ከእነርሱ ጋር የነበሩ ሁሉ ነበርን አይተናል ብለው አውርሰውት ከሔዱና ሁሉም እየተቀባበለ ለእኛ ካደረሰው በኋላ እናንተ አንቀበልም በማለታችሁ ከሐዋርያት መንገድ መውጣታችሁን ታረጋግጡልናላችሁ እንጂ እኛ የምንጠራጠር ይመስላችኋልን?የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት ትውፊት ወይም የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት የማትቀበሉ ከሆነ ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን ከየት አገኛችሁት? ማን ሰጣችሁ? ምዕራፍና ቁጥሩንስ ከየት ተቀበላችሁት? ነቢያት ሐዋርያት እንደጻፉትስ በምን ታረጋግጣላችሁ? በእነማንስ በኩል ተጠብቆ ደረሳችሁ? ለመሆኑ ተነሣች ዐረገችን ለመቀበል ከቸገራችሁ አልተነሣችም አላረገችምን ለምን አመናችሁት? የተነገረውንና ሲተላለፍ የኖረውን ለማመን የምትቸገሩ እናንተ ልብወላዳሁን ለማመን የሚያፋጥናችሁ ማን ነው? መቼና እንዴት እንደተፈጸመ ወይም የዕረፍቷንና የአቀባበሯ ሌላ ትውፊት እንኳ ሳትይዙ የነበረውን ለማቃለል ብቻ የሚያጣድፋችሁ እንዴት ያለ ክፉ መንፈስ ነው? እናንተ የተረጋገጠ ጽሑፍ ብቻ ነው የምንቀበልስ ካላችሁ ትንሣኤና ዕርገቷ የተመለከተውን ጽሑፍ ማን እንደጀመረው፣ እንዴት እንደተሸጋገረና እንዴት ስሕተት እንደሆነስ ለምን አልመረመራችሁም? ጥላቻ ጊዜ አይሰጥማ፤ ክህደት የእውነተኛ ዐውቀት ጭላንጭል የለውማ፡፡ እንግዲህ እናነተን በምን መርዳት ይቻል ይሆን? ሐዋርያትን ካልተቀበላችኋቸው እኛንማ እንዴታ!በክህደት ትምህርታችሁና በስም ማጥፋታችሁ የምንደነግጥ ይመስላችኋልን? ይህንማ ሥራችሁ እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ እናንተም ሥራችሁን እኛም ሥራችንን እንሠራለን፡፡ በኋላ ዘመን ዋጋችን እንደ ሥራችን እንዲመዘን እናውቃለንና፡፡ ወይስ እንደ ዲያብሎስ ተስፋ ድኅነት የለንም ብላችሁ ተስፋ ቆረጣችሁ
ትንሣኤዋና ዕርገቷ ለክርስቲያኖች ሊቀበሉት የማያስቸገረው ግን የተረጋገጠ ትውፊት በመኖሩ ብቻም አይደለም፡፡ ትልቁና ዋናው ምሥጢር ያለው ደግሞ እመቤታችን ‹‹ ልዩ ›› መሆኗ ላይ ነው፡፡ ዕድገቷና ሕይወቷ ልዩ ነበር፡፡ በእርሷ የተደረገው የአካላዊ ቃል ጽንስና ወሊድም እስካሁን  ሊገልጹት ቀርቶ ሲያስቡትም ይከብዳል፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹‹ ይህንም ባሰብኩ ጊዜ ኅሊናዬ የልጅሽን የባሕሩን ጥልቅነት ሊዋኝ ይወዳል፤ የወዳጅሽ የመሰወሪያው ማዕበልም ያማታዋል፡፡ ... አሁንም ገናንቱን አንመርምር፤ ጥልቅነቱንም አንጠናቀቅ፤ የገናንቱን መጠን ለማመስገን የነቢያትና የሐዋርያት አንደበት የማይቻለው ነው›› እንዳለው ለማንም የሚቻል አይደለም፡፡ ለዚህ የታደለችው ነገሩን ሁሉ በልቧ ትጠብቀው የነበረችው እራሷ ድንግል እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ገብርኤልም ቅድስት ኤልሳቤጥም ‹‹ ልዩ›› መሆኗን አስቀድመው ምስጋናቸውን ያስከትሉላት፡፡ ታዲያ እመቤታችን ልዩ በሆነ መንገድ ከጸነሰችና ከወለደች ልዩ በሆነ መንገድስ የማትነሣው የማታርገው ለምንድን ነው? መነሣቷና ማረጓ አድሎ ያስመስላል የሚባለው በድንግልና ጸንሳ በድንግልና መውለዷንስ ለምን አድሎ ነው አይባልም? ጽንሱ ልደቱ ሰለ እርሱ ነው የምትሉ ከሆነስ ትንሣኤውና ዕርገቷ ምን የሚያረጋግጥ ይመስላችኋል? የእርሱን ትንሣኤና ዕርገት ተሰርቆ ነው ሲሉ የነበሩ አይሁድ በእርሷ ትንሣኤና ዕርገት ሲያፍሩ ብዙዎቹም ከእነርሱ ወደ ክርስትና ሲመለሱ እናንተ ይህን ከማለት የማትመለሱ የክርስቶስን ትንሣኤም ሳታውቁ ታቃልላላችሁን? የእናንተ ክሳደ ልቡና በእውነቱ እንደምን ከዚያ ዘመን አይሁድ ይልቅ ጸና? በውኑ አድሎን ለእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት የምትጠቅሱት በደብረታቦር በዓል ሙሴን ከሙታን ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሦስቱን ብቻ ይዞ መውጣቱንስ አድሎ ትሉታላችሁን? በእውነቱ ስንቱን ተመሳሳይ ታሪክ ልንጠቅስ ስንቱንስ ልናስታውሳችሁ እንችላለን? በእውነት የቀደሙትን አበው ትምህርትና ትውፊት እንዳትቀበሉ የእግዚአብሔርንስ የማይታወቅ መንገድ የደረሳችሁበት አስመስሎ ያሞኛችሁ ወይንም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? የእመቤታችን ልዩ መሆን ካልገባችሁ በትንሣኤዋና በዕርገቷም ልዩ መሆኗን እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? ማስተዋላችሁን የጋረደውን የስድብና የስም ማጥፋት ግብር ያሰደረባችሁን ከፉን መንፈስ ትቃወሙትና ከዚህም ነጻ ትወጡ ዘንድ በእውነት እግዚአብሔር ይርዳችሁ ከማለት በቀር ምን ልንል እንችላለን፡፡ድንግልማ በእውነት ተነሥታለች ዐርጋለችም፤ ክብር ምስጋና ለተወደደ ልጇ ይሁን፤ አሜን፤ በረከቷም ይደረብን፡፡

አርምሞትኪ ማርያም ኃለፈ እም አንክሮ፤
እስከ ንሬኢ ሕዝብኪ ለተአምርኪ ግብሮ፤
ገነትኪ ትጽጊ ሰላመ ወተፋቅሮ፤
እለያማስኑ ለዓጸደ ወይንነ ወፍሮ፤
ቆናጽለ ንዑሳነ አፍጥኒ አሥግሮ፡፡

© ከዲ/ን ብርሃኑ አድማስ መጽሐፈ ገጽ በቀጥታ የተወሰደ!!!