2013 ማርች 30, ቅዳሜ

እንኩዋን ለመስቀሉ ስር እናታችን ለቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያም ወርሃዊ በአል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን !!! ጥያቄየ፡- እግዚአህሄር ኤልሻዳይ ነዉ ያድርበት ዘንድ የወደዳትን ዘር ማስቀረት አይችልምን ደግሞስ አምላክ ከመጀመሪያዉ ማደሪያዉ ትሆን ዘንድ ለይቶ ያለሃጢያት የጠበቃትን ጉድፍ የሌለባትን የሰርግ ቤት አድፋ ነበር ማለት የሚቻለዉ ማን ነዉ፡፡ ከዘሯ የቀሩትን የእየሱስ ምስክርነት ያላቸዉን ሊዋጋ በባርህ አሽዋ ላይ ከቆመዉ በቀር ይቃወማት ዘንድ ማን ይደፍራል ? ለሁላችንም ማስተዋሉን አምላካችን ያድለን የዚህ ጽሁፍ መልእክት ድንግል ማርያምን ጥንተ አብሶ አላገኛትም የሚል ነው ፡፡ ምናልባት ይኸ መልስ በተለያየ ጊዜ የተነሱትን ጥያቄዎች ሁሉ ለመመለስ ይሞክራል ተብሎ ይገመታል፡፡ 1. አንዳንዶች፡- ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ የጠፋላት መልአኩ ባበሠራት ጊዜ ነው በማለት ይጽፋሉ፡፡ ይህ አባባል ከዚህ በፊት መልአክ ያበሠራቸው ማኑሄና ሚስቱ ፣ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ለምን ጥንተ አብሶ አልጠፋላቸውም ያሰኛል ? መሳ 13.2-3 ፣ ሉቃ 1.13 ፡፡ ጥንተ አብሶ የሚጠፋው በብሥራተ መልአክ ቢሆንማ ፣ አካላዊ ቃል ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ፣ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው በመሆን ፣ መከራ መቀበልና ፣ በመስቀል ላይ መሞት አያስፈልገውም ነበር ፡፡ በቀላሉ ውርደትንና ሞታችንን ሳይካፈል ፣ እልፍ አዕላፋት መላእክትን ልኮ ብሥራትን በመንገር ብቻ ጥንተ አብሶን ከሁላችንም ዘንድ ማጥፋት ይቀለው ነበር ፡፡ በሌላ በኩልም ፣ የቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ከጥንተ አብሶ ነጻ ማድረግ ከቻለ ፣ የአንድ መልአክን የብሥራት ቃል ከክርስቶስ ደምና ሞት ጋር እኩል አድርገነዋል ማለት ስለሚሆን ፈጽሞ የተሳሳተ መግለጫ ነው ፡፡ 2. አሁንም ሌሎች ደግሞ ጥንተ አብሶ የጠፋላት ፣ ጌታ በሚፀነሰበት ወቅት ፣ ከመቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ሲጸልላት ነው ይሉናል፡፡ ይህም ጌታ ሰው መሆን ያስፈለገውና ወደ እዚህ ምድር የመጣው አዳማዊውን በደል ማለትም ጥንተ አብሶን እንዴት አድርጐ ለማጥፋት ነው? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል ፡፡ መልሳችንም በመስቀል ላይ በሚፈጽመው ቤዛነትና በሚከፍለው መሥዋዕትነት ብቻ ነው የሚል ነው ፡፡ እንግዲህ እመቤታችን ጥንተ አብሶ ከነበረባት ፣ መድኃኒቴ ያለችውንም ቃል አጣምረን ደምረን ፣ እንደማናቸውም ሰው በመስቀል ላይ በሚፈጸም ቤዛነት ብቻ ከጥንተ አብሶ መዳን ነበረባት እንጂ ፣ አንዳንዶች እንደሚሉት መንፈስ ቅዱስ በጸለለባት ጊዜ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ንጽህና ከሌለ ደግሞ ጌታ የተጸነሰው ጥንተ አብሶ በነበራት አንዲት ሴት ማህጸን ነው ስለሚያሰኝ ፍጹም ስህተት ይሆናል(1) ፤ በመቀጠልም የዳዊት መዝሙርን እንደሚተረጉሙት ጌታችንንም በኃጢአት ተወለደ ሊያስብል ነውና(2) ፡፡ በሌላው ወገን ደግሞ መንፈስ ቅዱስም በበኩሉ ጥንተ አብሶን አንጽቶ ድህነትን የሚያስገኝ ከሆነ ፣ በዚህ ዓለም ላለነው የአዳም ልጆች ሁሉ ፣ ሁለተኛ አማራጭ የመዳኛ መንገድ አለን ብለን ልንመሰክር ነው ማለት ነው(3) ፤ ማለትም በኢየሱስ ሞትና ደም ሌላም በመንፈስ ቅዱስ መጽለል በኩል፡፡ ሎቱ ስብሐት !!! የፈሰሰውን ደም ፣ ስለ እኛ የተቀበለውን ፍዳና መከራ መካድና ተደራራቢ ስህተቶችን ማምጣት ፡፡ 3. ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ ወደ እመቤታችን በመጣ ጊዜ ፡- “ደስ ይበልሽ ፣ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው ፤ ከሴቶች መካከል አንቺ የተባረክሽ ነሽ ፡፡” በማለት አመስግኗታል (ሉቃ 1.28) ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ፣ ከእርሷ በፊት ይህን በሚመስል ምስጋና የተመሰገነ አንድም ፍጡር የለም ፡፡ ይኸ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእመቤታችን የተሰጠ ምስጋና ነው ፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር !!! እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጥንተ አብሶ ተይዛ ቢሆን ኖሮ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “ጸጋን የተመላሽ ሆይ” ሊላት አይችልም ነበር፡፡ ምክንያቱሳ ቢሉ ፣ ጥንተ አብሶ ጸጋዋን ጐደሎ ያደርግባት ነበርና ነው፡፡ አዳም በደልን እንደ ፈጸመ በቀጣዩ ያጋጠመው የመጀመሪያው ቅጣት ጸጋው መጉደሉ ወይም መገፈፉ ነው ፡፡ ይኸ የአዳም በደል አለባት ከተባለ ፣ ጸጋዋ እንደ ቀደም አባቷ መጉደል ይገባው ነበርና ፣ ታድያ መልአኩ እንዴትና ስለምን ኦ ምልአተ ጸጋ በማለት ሊያወድሳት ይችላል? 4. ሌሎች ደግሞ ሉቃ 1፡47 የተነገረውን ድንግል ማርያም በራሷ ላይ የምስክርነት ቃል እንደ ሰጠች አድርገው በማቅረብ ጥንተ አብሶ እንደነበረባት ለማስረዳት ይሞክራሉ ፡፡ ይኸን ቃል ለመናገር የሚገደደው ፍጡር የሆነ ሁሉ እንጅ አዳማዊ ኃጢአት ያለበት ብቻ እየተመረጠ አይደለም ፡፡ በአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አምሳል የተፈጠረ ፍጡር በሙሉ አምላኬ ፣ መድኃኒቴ ፣ በማለት አምላኩን ያወድሳል፡፡ ድንግል ማርያም በተለየ መድኃኒቴ የሚለውን የምስክርነት ቃል የሰጠችው ፣ ገና ኢየሱስ ሳይወለድና በመስቀል ላይ ሞቶ ሳያድናት ነው ፡፡ ሳይሞትና መስዋዕት ሳይሆን ደግሞ ስለድኀነት መናገር ስለማይቻል ፣ ከፍጥረት አስቀድማ ድና ነበር ያሰኘን እንደሁ እንጅ ፣ ገና ደሙን ያላፈሰሰና ያልሞተውን አምላኳንና ልጅዋን ፣ ሰው መሆኑን እንኳን አይታ ያላረጋገጠችውን የማህጸን የጽንስ ፍሬ መድኃኒቴ ብላለች በማለት ያልሆነ ትርጓሜም በመስጠት ወይም የትንቢት ቃል አስመስሎ መከራከር ፣ የሚያስኬድ ሆኖ አላየሁትም ፡፡ ከመስዋዕትነት በኋላ የተነገረ ቃል ቢሆን እንኳን ፣ ያንን ተንተርሶ ትንሽ ለማደናገር ክፍተት ይገኝ ነበር ፡፡ ቤዛነቱ ሳይፈጸም መድኃኒቴ ስላለች ፣ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በተለየ መንገድ ድናለች ወይም ቀድሞውንም ከጥንተ አብሶ ጠብቆ አቆይቷቷል ፣ ለማለት እንደፍራለን እንጅ አዳማዊ በደል አግኝቷታል የሚለው በየትም በኩል ማስማሚያ የለውም ፡፡ እግዚአብሔር ነቢይ ሊያደርግ የፈለገውን እንኳን “በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ” እያለ የተናገረ / ኤር 1፡5/ ፤ ለማደሪያውና እናት ትሆነው ዘንድ የመረጣትን ቅድስትና ብፅዕትማ ደግሞ ፣ ምን ያህል እንደ ሚጠበብላትና እንደ ሚያሰናዳት ባለ አእምሮ የሆነ ሰው ሁሉ ሊያጤነው ይገባል ፡፡ ከልማደ እንስትና ከሀልዮ (ሃሳብ) ፣ ከነቢብና (ንግግር) ፣ ከገቢር (ሥራ) ኃጢአት ነጻ ያደረጋት ፈጣሪ ጥንተ አብሶን አላስወገደላትም ማለት ፈጽሞ ቧልት ነው ፡፡ 5. ኢሳ 1፡9 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር የሚለውን ስለይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ህዝብ እንደተነገረ አድርገው የሚተረጉሙ አሉ ፡፡ ከቁጥር 9 ንባብ አስቀድሞ በቁጥር 8 ላይ ስለ ጽዮን ሴት ልጅ የሚናገረውንስ እነዴት መንደርና ከተማ አድርጐ መተርጐም ይቻላል ? ኢሳይያስ ነገሩን እያጠራልን ሲሄድ በምዕራፍ 2 ላይ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም እየተናገረ በቁጥር 2 ስለ ዘመን ፍጻሜ ክስተት ያወሳናል ፤ በቁጥር 3 ደግሞ ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል (አጽንኦት) ከኢየሩሳሌም ይወጣል ፤ ለአሕዛብ ሁሉ መንገዱን ያስተምራል ፣ በጎዳናውም እንደሚሄዱ ይናገራል ፡፡ እንዲያውም ዳግም አትታወሩ ብሎ ሊያሳርፈን ሲፈልግ ፣ አለፍ ብሎ በምዕራፍ 7፡14 ደግሞ ለዳዊት ቤት እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች ፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች ይልና ፣ ትንቢቱን ያስቀምጥልናል ፡፡ በመቀጠልም በምዕራፍ 9፡6 ደግሞ ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል በማለት የምትወልድውን ህፃን ማንነት በግልጽ ያበሥራል ፡፡ ስለዚህም መጽሐፉ የሚነግረን መንፈስ ቅዱስ በምዕራፍ 1፡9 ፤ 2፡2-3 ያስረዳውን ስውር ቃል በምዕራፍ 7፡14 ግልጽ እንደ አደረገለትና ፤ ይህንኑ የተስፋ ቃል ደግሞ በማቴዎስ 1፡18 በእውን እንደ ተረጐመው ነው፡፡ በመሆኑም ከመጀመሪያ ምዕራፍ አንስቶ በተደጋጋሚ በተለያየ ሥፍራ ስለ ድንግል ማርያም ተናግሯልና በኢሳ 1፡9 የተገለጸውም እሷን የሚመለከት ቃል ነው እንጅ ስለ አገርና ህዝብ የተነገረ አይደለም ፡፡ 6. ደግሞም ወንደ አላዉቅም አለች እንጂ ጥንተ አብሶ ስላለብኝ እንዴት ይሆንልኛል አላለችም፡፡ መልአኩም እንደምትጸንስ የልኡል እግዚብሄር ልጅ እግዚአብሄርን እንደምትወልድ እርሱም ታለቅ እንደሆን በዳዊት ዙፋ እንደሚቀመጥ ለመንግስቱም ፍጻሜ እንደሌለዉ ሲነግራት እንደሰዉ ልማድ ስለመሰላት ወንድ አላዉቅም አለችዉ በዚህም እንኳንስ በስጋዋ በሃሳቧም ንጽህት እንደሆነች እንረዳለን ባጠገቧ ያለዉን ዮሴፍን እንኳን አላሰበችምና፡፡ ከዚህ በኋላ ነዉ እንግዲህ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል የልዑል ሃይልም ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ካንቺ የሚወለደዉ ቅዱስ የእግዚበሄር ልጅ ይባላል ያላት ፡፡ ወንድ አላዉቅም ማለት ያለወንድ ዘር መዉለድ አይቻልም እኔ ደግሞ እንዲህ የማድረግ ሃሳብ ፈጽሞ የለኝም የሚል ትርጉም የሚሰጥ እንጂ ሃጢያተኛ ነኝ የሚል ትርጉም የለዉም፡፡ ለዚሀም ነዉ የምትወልደዉ ያለወንድ ዘር እንደሆነ ‹‹ መንፈስ ቅዱስ ባንችላይ የመጣል የልዑል ሃይልመ ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንች የሚወለደዉ ቅዱስ የእግዚብሄር ልጅ ይባላል ያላት፡፡ለመሆኑ መንፈስ ቅዱስ ስራዉ ማንጻት ብቻ ነዉ እንዴ ሃዋሪያት እኮ መንፈስን ቅዱስን እስክልክላችሁ ድረስ ከእየሩሳሌም እንዳትወጡ የተባሉት ቅዱሱ መንፈስ ካላጸናቸዉ በቀር የእዉነትን ቃል መሸከም ስለማይችሉ ነዉ፡፡ ማርያም ደግሞ ልትሸከም የተመረጠችዉ የቃሉን ባለቤት ነዉ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ያጸናጽ ዘንድ እንጅ ያነጻት ዘንድ እንዳልሆን እናስተዉል ፡፡ ደግሞም የልኡልም ሃይል ይጸልልሻል (ይጋርድሻል) በማለት የተጋረደች የንጉስ መንበር እንደምትሆን ነገራት እንጅ ፈጽሞ ስለ ሃሚያት መንጻት መልአኩ አልተናገረም፡፡ ለአባ ሕርያቆስ ፤ለቅዱስ ኤፍሬም ፤ለቅዱስ ያሬድ ፤ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተገለጸች ዕመቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት ትጎብኘን ፤ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን -አሜን ወስብሐት ለእግዚአብሔር —

2013 ማርች 29, ዓርብ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!!!

የቅድስት አርሴማ ጦማር


ወንድሞችና እህቶች እንደምን አላችሁ? እነሆ በቸሩ ፈጣሪያችን በእግዚአብሔር ፈቃድ ጡመራችንን አሀዱ ብለን ጀምረናል እግዚአብሔር ሁላችንንም ይርዳን አሜን!!!!

2013 ማርች 28, ሐሙስ

“ስለእኛ ሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ሮሜ 8፡34 ብዙ ጊዜ ብዙ ወገኖቻችን ይህንን ጥቅስ በመያዝ ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅ ነው ከእርሱ ውጪ ማንም ስለእኛ እግዚአብሄርን የሚለምንልን የለም ይላሉ ቃሉም እንዲህ ሲል ይጀምራል “እግዚአብሄር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል” ይህ ማለት እግዚአብሄር ተከተሉኝ ብሎ በመጥራት የመረጣቸውን አይ እነርሱ አንተን ሊከተሉ አይገባቸውም ሊመረጡም አይችሉም ብሎ የሚከሳቸው ማን ነው ? በማለት ይጠይቃል በመቀጠልም “የሚያጸድቅ እግዚአብሄር ነው” በማለት የመረጣቸውን ሰዎች መንግስቱን ለማውረስ እናንተ የአባቴ ብሩካን ብሎ የሚያጸድቃቸው እግዚአብሄር ነው አለ እንዲሁም “ የሚኮንን (የሚፈርድ ) ማነው ” በማለት ይጠይቃል ፡፡ “መኮነን ” ከግእዙ ሳይተረጎም ቀጥታ የተወሰደ ቃል ሲሆን መኮነን ማለት መፍረድ ማለት ነው ምክንያቱም “ኮነነ” ከሚለው የግእዝ ስርወ ቃል የወጣ ሲሆን “ኮነነ” ማለት ደግሞ ፈረደ ፣ገዛ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ማጽደቅና መኮነን የአማላጅነት ስራ ሳይሆን የፈራጅነት ስራ እንደሆነ ልብ እንበል በመቀጠልም “የሚኮንንስ ማነው ?” ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ቁጥር 34 ላይ “የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሳው በእግዚአብሄር ቀን ያለው ” በማለት አሁን ያለበትን የእግዚአብሄርነት የስልጣን ስፍራ ይገልጻል ፡፡ የሞተውና ሞትን ድል አድርጎ በስልጣኑ የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሄር ቀኝ ( በእግዚአብሄርነት ስልጣን) አለ ማለት ነው፡፡ መቼም እግዚአብሄር ቀኝና ግራ ፊትና ኋላ እንደፍጡር የለውም እርሱ ስፍራ የማይወስነው ረቂቅ ነው የነፋስን ቀኝና ግራ የሚያውቅ ማነው ? ከነፋስ ይልቅ ነፍስ ትረቃለች ከነፍስ ደግሞ መላእክት ይረቃሉ ከመላእክት የበለጠ ደግሞ እግዚአብሄር ይረቃል ስለዚህ እግዚአብሄር በአለም ሁሉ ምሉእ ነው ፡፡ ታዲያ በእግዚአብሄር ቀኝ ሲል ምን ማለት ነው ? ብለን ስንጠይቅ በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ቀኝ የተለያየ ትርጉም ቢኖረውም በዚህ ምእራፍ ላይ ግን ክብርን ፣ስልጣንን ያመለክታል ፡፡ በመዝ 117፡16 ላይ “የእግዚአብሄር ቀኝ ሃይልን አደረገች ” ይላል ይህ ማለት እግዚአብሄር በስልጣኑ ኃይልን እንዳደረገ የሚገልጽ ነው ምክንያቱም እግዚአብሄር ኃይልን የሚያደርገው ሰዎችንም ከፍ ከፍ የሚያደርገው በስልጣኑ በመለኮታዊ ኃይሉ መሆኑ ግልጽ ነው :: በመሆኑም የእግዚአብሄር ቀኝ ሲል ስልጣኑን (መለኮታዊ ክብሩን ) ያመለክታል፡፡ በዘጸ 15፡12 ላይ “ቀኝህን ዘረጋህ ምድርም ዋጠቻቸው ” ይላል ከዚህም የምንረዳው ግብጻውያንን እግዚአብሄር በስልጣኑ ምድር እንድትውጣቸው ማድረጉን ነው፡፡ ስለዚህ “በእግዚአብሄር ቀኝ ያለው ” ማለቱ በስልጣንና በክብር በሰማያት ያለው ማለቱ ነው፡፡ ይህም ማለት ክርስቶስ ቀድሞ ስጋ ከመልበሱ በፊት ክብር የሌለው ሆኖ በኋላ ክብር አገኘ ለማለት አይደለም ክብርና ስልጣኑ ቅድመ ተዋህዶ ጊዜ፣ ተዋህዶ ፣ድህረ ተዋህዶ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ነው ፡፡ በመቀጠል እንዲህ ይላል “በእግዚአብሄር ቀኝ ያለው ደግሞም ስለእኛ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ” በክፍት ቦታው ላይ ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ሙሉ ብንባል ያለጥርጥር የምንሞላው የሚፈርደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው የሚለውን ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ በዝርዝር እንዳየነው ጥቅሱ የሚያመለክተው ፈራጅነቱን እንጂ አማላጅነቱን በፍጹም አይደለም ፡፡ ማጽደቅና መኮነን ከቻለ እንዲሁም በእግዚአብሄር ቀኝ (ክብር) ካለ እርሱ ክርስቶስ ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይሆንም፡፡ ደግሞ “የሚኮንን ማነው ?” የሚለውና “ስለእኛ የሚማልደው ” የሚሉት ሁለት ቃላት (ሃሳቦች) እርስ በእርሳቸው እንዳይጋጩ አስማምቶ መተርጎም ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ልንረዳ የሚያስፈልገው ነጥብ “የሚኮንንስ ማነው የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሳው በእግዚአብሄር ቀኝ ያለው ደግሞ ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ” ያለው ለትስብእት ነው ምክንያቱም ትስብእት (ስጋ) መለኮት ስለተዋሃደ ቢሞትም ከሞት በሃይል ተነሳ መነሳት ብቻም አይደለም የመለኮት ገንዘብ ለስጋ ገንዘቡ ስለሆነ እግዚአብሄርነትን አግኝቶ አሁንም በእግዚአብሄር ቀኝ ማለትም በእግዚአብሄርነት ክብር አለ ደግሞም ስለእኛ ይማልዳል እዚህ ላይ ልብ እንበል ስለእኛ የሚማልደው ሲል አሁን ስጋ በሰማይ የተዋሃደውን መለኮት እየወደቀ እየተነሳ እያነባም የሚማልድ የሚለምን ነው ማለት አይደለም በስጋው ወራት ማለትም በዚህች ምድር በፈጸመው የአንድ ጊዜ ልመና አሁንም ድረስ የሚያድን መሆኑን ሚገልጽ ነው ፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ስለእኛ የሚማልደው ” የሚለውን ቃል ይዘው አሁንም እየወደቀ እየተነሳ የሚማልድ ነው ብለው የሚያስቡ አሉ …አይደለም የመስቀሉን ምልጃ ነው አሁን የሚደረግ አስነስሎ የጻፈው ፡፡ ለምሳሌ ጌታ ከመወለዱ ከ 700 አመታት በፊት የነበረው ኢሳይያስ በትንቢቱ መጽሃፍ ላይ ስለጌታ የእለተ አርብ እንግልት ሲጽፍ እንዲህ አለ “ከአመጸኖች ጋር ተቆጥሯል ….ስለአመጸኖች ማለደ ” ይላል ኢሳ 53፡12 አሁን ይህን ቃል ስንመለከተው ያለፈ ድርጊት ነው እንጂ ወደ ፊት የሚፈጸም ድርጊት አይመስልም ኢሳይያስ ግን በዘመኑ እየተናገረ ያለው ወደፊት ከ 700 አመታት በኋላ ጌታ ላይ ስለሚደርሰው መከራና የማዳን ስራ ነበር፡፡ ቅዱስ ዳዊትም “እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ አጥንቶቼ ሁሉ ተቆጠሩ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም ልብሶቼንም ለራሳቸው ተከፋፈሉ በቀሚሴም ላይ እጣ ተጣጣሉ ” ይላል ፡፡ መዝ 21፡16-18 መዝሙረኛው ዳዊት በዘመኑ ወደፊት ሚሆነውን እንደ ክርስቶስ ሆኖ ይናገር ነበር ከ 800 አመት በኋላ ሚሆነውን የጌታ ስቃይ እርሱ ግን እንደሆነ አድርጎ መግለጹ ስህተት እንዳልሆነ ሁሉ የተፈጸመውን ወደፊት እንደሚፈጸም አድርጎ ቅዱስ ጳውሎስ “ስለእኛ የሚማልደው ” ብሎ ቢገልጸውም ትክክልና የመጽሃፍ ቅዱስ ዘይቤ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ዛሬም ክርስቶስ በሰማይ እየወደቀ እየተነሳ ይማልዳል ብሎ ማሰብ በዚህ ምድር ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የፈጸመውን የማዳን ስራ እንዳልተሟላ በሰማይም የሚቀጥል አድርጎ መቁጠር ነው፡፡ ይህንን እንዳንል ደግሞ ክርስቶስ እራሱ በመስቀል ላይ በመጨረሻው ሰአት ላይ “ተፈጸመ ” ብሏል ፡፡ ዮሃ 19፡ 30 ቅዱስ ጳውሎስም በ2ኛ ቆሮ 5፡16 ላይ “ክርስቶስን በስጋ እንደሆነ ያወቅነው እንኳን አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ በስጋ አናውቀውም ” ብሏል ይህም ማለት ክርስቶስ ስጋን እንደተዋሃደ ቢያርግም አሁን ግን በስጋ የሚማልድ ፣ሚወድቅ፣ የሚነሳ በምድር ላይ ሲያደርግ እንደነበረው የሚያነባ አይደለም በክብር ዙፋኑ ተቀምጦ የሚፈርድ ነው እንጂ፡፡ መጽሃፍ እንዲህ ይላል “ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለን” ሮሜ 14፡10 “ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናል ”2 ቆሮ 5፡10 ፣ዮሃ 5፡ 22 “ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው ” ክርስቶስ ከእርገቱ በኋላ በምድር ሲያደርግ እንደነበረው የመለመን ፣የመማለድ አገልግሎት እንደማይፈጽም እንዲህ ሲል ተናግሯል “እኔም ስለእናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም ፡፡” ዮሃ 15፡25 ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈርዳል እንጂ አይማልድም፡፡ ነገር ግን ብዚህ መልኩ መጽሃፍን ካልተረዳን "ይማልዳል" የሚል ቃል የያዙ በመሆናቸዉ ብቻ አማላጅ የሚል ትርጉም ከሰጠን ወደ አልሆነ ምንፍቅና ይወስደናልና እንጠንቀቅ። ለዚህ ማስረጃ የሚከተሉትን ጥቅሶች መመልከት ይቻላል:- ሮሜ ምዕራፍ 8፡ 26 – 27 እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና። /ግንዛቤ መንፈስ ቅዱስ ይማልድልናል/ ሮሜ 8፡34 የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። /ግንዛቤ ኢየሱስ ይማልዳል/ ኤር 7 ፡23-25ነገር ግን። ቃሌን ስሙ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ መልካምም ይሆንላችሁ ዘንድ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ በዚህ ነገር አዘዝኋቸው። ነገር ግን በክፉ ልባቸው አሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደ ፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም። አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር። /ግንዛቤ እግዚአብሔርም ይማልዳል/ እነዚህን ሦስቱንም ኃይለ ቃሎች አስማምተንና አስታርቀን ለመጠቀም እንድንችል በጸሎታችን ማለት የሚገባን አብ ፣ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አማልዱን ማለት ሊያስፈልግ ይመስላልና ።ይህ ደግሞ ታላቅ ስህተት ነዉ።ስለዚህ አንድ ቃል በመያዝ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይብቃ እንላለን። ወስብሃት ለእግዚአብሄር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ይትአኮት ወይሴባህ ስሙ ለእግዚአብሄር ወትረ በኩሉ ጊዜ ወበኩሉ ሰአት አሜን።

╬ ╬ ╬ ወዘሕጎ ፡ ያነብብ ፡ መዐልተ ፡ ወሌሊተ~~~ +~~ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል ╬ ╬ ╬ ብፁዕ ፡ ብእሲ ፡ ዘኢሖረ ፡ በምክረ ፡ ረሲዓን ፤ወዘኢቆመ ፡ ውስተ ፡ ፍኖተ ፡ ኃጥኣን ፤ ወዘኢነበረ ፡ ውስተ ፡ መንበረ ፡ መስተሳልቃን ።ዘዳእሙ ፡ ሕገ ፡ እግዚአብሔር ፡ ሥምረቱ ፤ ወዘሕጎ ፡ ያነብብ ፡ መዐልተ ፡ ወሌሊተ ።ወየከውን ፡ ከመ ፡ ዕፅ ፡ እንተ ፡ ትክልት ፡ ኀበ ፡ ሙሓዘ ፡ ማይ ፤ እንተ ፡ ትሁብ ፡ ፍሬሃ ፡ በበጊዜሃ ።ወቈጽላኒ ፡ ኢይትነገፍ ፤ ወኵሎ ፡ ዘገብረ ፡ ይፌጽም ። ~~~~~~~~~~~~~ ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። መዝ 1፣1

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!!! ወንድሞችና እህቶች እንደምን አላችሁ? እነሆ በቸሩ ፈጣሪያችን በእግዚአብሔር ፈቃድ ጡመራችንን አሀዱ ብለን ጀምረናል እግዚአብሔር ሁላችንንም ይርዳን አሜን!!!!