2013 ኤፕሪል 10, ረቡዕ

+++++++++ኦርቶዶክስ ተዋህዶ +++++++++

 +++++++++ ተዋህደ ስንል ምን ማለት ነው? +++++++ ያ ቅድመ አለም ከአብ ዘንድ የነበረው ወልድ/ቃል/ ከድንግል ከስጋዋ ስጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ተወለደ። የሐ.1፤14 ያ ቃል ስጋ ሆነ። እንዲል። ቃል ስጋ ሆነ ሲባል ተለዉጦ ስጋ የሆነ አይደለም በቃና ዘገሊላ ወሓው ወደ ወይን ተጅ እንደተለወጠው ቃል ወደ ስጋነት አልተለወጠም። ወይም በልብስ ላይ ልብስ እንደሚለበሰው በቃል ላይ ስጋ አልተደረበበትም። መለኮትም ስጋን አላጣፋውም ስጋም መለኮትን አልዋጠውም።አንድ ብረት በእሳት ውስጥ ቢጨመር ብረቱ ቅርጹን ሳይለቅ የእሳትነትን ባህርይ እንደሚይዝ ስጋ የመለኮትን ባህርይ ገንዘብ አደረገ። እሳቱ በብረቱ በማደሩ ቅርጽ እንደሚወጣለት መለኮት ከስጋ ጋር በመዋሀዱ ታየ ተዳሰሰ ተኛ ተነሳ ተባለ።ይህ የወልድ ሰው መሆን ምስጢር ታላቅ ነው። እንደምስ የረቀቀ ነው።ሐዋርያው ለዚህ ነው ይህ ሚስጢር ታላቅ ነው። እግዚአብሔርን መምስል ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው ያለው።1ኛጢሞ 3፤17 ዓለም የዳነው በተዋህዶ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ተዋህዶን ለማብራራት የሚከተለውን የክርስቶስ ትምህርት እንውሰድ፡ እውነት እውነት እላችሗለሁ ስጋየን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ህይወት አለው። ዮሐ 6፤55 ይህ ቃል እንዲሚያስረዳን ስጋውና ደሙ የዘለዓለም ህይወትን ለማግኘት ወሳኝ መሆኑን ነው። ታዲያ ስጋውና ደሙ ከማርያም የተገኘ የሰው ስጋ ነው። የሰው ስጋ ደግሞ ብቻውን ሊያድን አይችልም ኢንዲያውም ሊያም ይችላል። መለኮት ደግሞ ስጋ የለውም። ስለዚህ ይህ ስጋና ደም በተዋህዶ የከበረ ነው እንላለን። ስጋን መለኮት ስለተዋሀደው አዳኝ አደረገው። መለኮት ስጋን ስለተዋሀደው የሚዳሰስ የሚጨበጥ አደረገው። በመሆኑም በተዋህዶ የከበረ ስጋውና ደሙ መዳኛ ሆነ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ