ሰኞ ፣14 ኦክቶበር 2013

ጠቃሚ ምክር

                                                                                          በዲ/ን ቃለአብ ካሣዬ

የቅድስት አርሴማ ጦማር
                                                                                    ‹‹ድልም ብዙ ምክር ባለበት ዘንድ ነው››  ምሳ. 24÷6
ተመክሮ አይድን አትበለው!

ወዳጄ ሆይ፡-እነሆ ጎበዝ ትሆን ዘነድ ሰነፍ አትሁን፡፡ ስንፍና ያለምንም ህመም አልጋ ያስይዝሃል፤ ለነገሩ አልጋ ያስያዘህ ስንፍና ራሱ በሽታ ስለሆነ ነው፡፡ ደግሞም ሰነፍ አልጋም ቢለቅ ሥፍራውን ሁሉ አልጋ ያደርገዋል፡፡ ጥንታውያን ሰዎች ‹‹ሰነፍ ካልሠራ፤ የለውም ሥፍራ›  ይላሉ፡፡ ሆኖም ‹‹ሰነፍ የሚሠራበት ሥፍራ ባይኖረው የሚጣላበት ሥፍራ አያጣም››፤የሚለው ንግርት ይፈፀም ዘንድ ነው ብዬ ልሣቅ እንጂ፡፡ አንዳንድ ቀናተኞች ስንፍና ይወገድ ዘንድ  በሰነፍ ጀርባ ላይ  በትር ሲያሣርፉ ኖረዋል፤ በትር ግን በሰነፍ ጀርባ ላይ ቄጤማ ነው፤ አይመክረውምና!!! ሰነፍን ያስተኛው ልቡ እያለ የተኛበት ጀርባው የሚገረፈው ስለምንድር ነው እላለሁ?

      ወዳጄ ሆይ ፡- ሰነፍ ቢሰንፍም ሰነፍን ለመምከር ግን አትስነፍ ‹‹ ሰነፍ ደስ እንዲለው በማይገባው አመስግነው!!! ከሚለው ብሂል ጋር እንዳትስማማ እለምንሃለሁ፤ ይልቁንም የሚገባውን ውቀሰው!!! ‹‹ ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም›› ይላልና አንተንም አታስፈልገኝም ቢልህ አትዘንበት (መዝ .13÷1):: ተመክሮ አይድን ነህ !አትበለው፤‹‹ ከሰነፍ ዝምድና፤ እጅ እግር የሌለው መልካም ቀን ይሻላል፤ ለሠው ጥግ ይሰጣልና›› ቢባልም  አንተ ግን ክርስቲያን ነህና ወዳጅነትህን አታቋርጥበት! አንተ ዘመድ ሁነውና የብርታት ጥግ ስጠው፡፡ ከሰነፍ ዘንድ ስንፍናን አትማር፤ እርሱ ግን ከአንተ ጉብዝናን ይማር ዘንድ በርታ፡፡ በረከትህ ይድረሰው እንጂ ርግማኑ አይድረስህ፡፡
ከሰነፍ አፍ የሐኬት እንጀራ እና ምክንያት አይጠፉምና ታገሠው፤ ሰነፍ የቆረሰውን እንጀራ አፉጋ እስኪያደርሰው ሲሠለቸውም ልታይ ትችላለህና ‹‹ ይህስ አይለወጥም!››አትበለው፤ አንተ ድከምለት እንጂ የሚለውጠው ሌላ ነው!!! ለሰነፍ የሚያዝን ሰው አስተዋይ ነው፤ የሰነፍንም እናት ከሀዘን ይታደጋታል፡፡ የመንታ እናት ተንጋላ ትሞታለች፤ የሰነፍን እናት ግን ሀዘን በቁሟ ይገድላታና፡፡ ( ምሳ. 7÷21 እና 25)፡፡ ሰነፍ ብትመክረው ወይ ይቆጣል አልያ ይስቃል፡፡ አንተ ግን ሳቁም ቁጣውም አይገድልህምና በቻልከው መጠን እርዳው፡፡ ወዳጄ እውነት እልሃለሁ ፤ሰነፍን ከመምከር ብዛት ትን ቢልህ ውሃ ጠጣ እንጂ ተስፋ አትቁረጥ! እግዚአብሔር የእኛ የሰው ልጆችን ደስታ የደበቀው ሠርተን በመድከማች ውስጥ እንደሆነ ሳትታክት ንገረው !ላባችን ውስጥ ፣ ጥረታችን ውስጥ ዕረፍት እንዳለ በትግዕስት ዘክረው! ጠቢቡ ሰለሞንም፡- ‹‹ሰው በሥራው ደስ ከሚለው በቀር ሌላ መልካም  ነገር እንደሌለ አየሁ፤ ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ያይ ዘንድ የሚመጣው ማን ነው?›› ብሎ እንደነገረን  ዘንድ ነው ( መክ .3÷22)፡፡ አዎ ወዳጄ፡- ሳይደክመው የሚያርፍ ሰነፍ ነውና ሰነፍን አበርታልኝ ፡፡የሰነፍ ግፍ ለገብስም ተርፎ ገብስም ሰነፍ ተባለ፤ ሰነፍ ገብስ ሲወቀጥ ገለባው ቶሎ ይለቀዋል፤ ሰነፍን ብትወቅጠው ግን ቶሎ ከስንፍናው አይገላገልምና ጽና፡፡
      ‹‹ ሰነፍን በሙቀጫ ውስጥ ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠው ስንፍናው በእርሱ አይርቅም››(ምሳ. 27÷22)፡፡ ከሰነፍ ሰው ሰነፍ ገብስ እንዴት ተሻለ?ብለህ እንዳትጠይቀኝ !አንዳንዴ እንዲህም ይሆናል፡፡
ነጮቹ ስንፍናን “the idea of doing nothing when things need doing” ይላሉ ደግሞም ‹‹Sign of weakness or shirking” ብለው ያክሉበታል፡፡
      አንዳንዴ ስንፍና ሊቋቋሙት የሚገባን ነገር መቋቋም መሰልቸት ነው፡፡ ስንፍና አለመቻል አይደለም፤ መቻልን አለመጠቀም ነው! የቀላልን ነገር ክብደት አምኖ መቀበል ነው! አሁን ማድረግ የሚቻለንን ‹‹አሁን አይቻለኝም ፤ነገ ነው የምችለው›› ማለት ነው፡፡ ሰነፍ- ነገም አሁን ሆኖ ሲመጣ ሌላ ነገን  ናፋቂ ነው፡፡ የአሁን ረሃብተኛ ፤የነገ ጥመኛ ሁለቱም ውስጥ ያልታደለ ነውና ሰነፍን በስንፍናው አውላላ ሜዳ ላይ አትለፈው፡፡ ብዙ የሥነ- ባህርይ አጥኚዎች ስንፍናን ለመርታት ተደጋጋሚ ፍቅር ተኮር ምክሮች ፣ ቅልጥፍናን የሚያነቃቁ ቀላል እንቅስቃሴዎችና፤ ተስፋን የሚፈነጥቁ ግልጽ የሕይወት ግቦችን ማስቀመጥ መልካም መሆኑን ያወሳሉ  እልሃለሁ፤ አንተም ወዳጄ ሆይ፡- ለሰነፍ ሰው የእውነት ወዳጅ ሁነው፤ አንተ ካልሆንህ ሌላ ማን ይሆነው ይሆን? እንኳን ሰነፍ ሰው ጎበዝም ሰው ወዳጅ ሲያጣ ይሞታልና፡፡የጥበብ ሰው አበባው መላኩ፡-

‹‹አባ ታጠቅ የቋራውም ፤
ስንቱን በግብሩ የሞገተ፤
አፍሎ ሥራይ ሳይበግረው፤
ለደብተራ ውግ ያቃተ፤፤
ለእንግሊዝ ክንዱን ሳያጥፍ፤
ስንቱን በሰይፉ እንዳልሸለተ፤
ተዋበች እንኳን፤
ስትሞት ችሎ፤
ገብርዬ ሲሞት ነው
የሞተ !!!››
     
      ብሎ የቀመመው ልቤን ይነካኛል፡፡ እናም ነው እኔ የምልህ፤ እናም ሰነፍ ጎበዝ እስኪሆን ድረስ ጐብዝ! የእግዚአብሔርም ፍቅር ከአንተ ጋር ጸንታ ትኖራለች!!! ‹‹ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው ፤ሰውን ሁሉ ታገሡ›› (2ኛ ተሰ .5÷14)፡፡