ቅዳሜ ፣30 ማርች 2013

እንኩዋን ለመስቀሉ ስር እናታችን ለቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያም ወርሃዊ በአል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን !!! ጥያቄየ፡- እግዚአህሄር ኤልሻዳይ ነዉ ያድርበት ዘንድ የወደዳትን ዘር ማስቀረት አይችልምን ደግሞስ አምላክ ከመጀመሪያዉ ማደሪያዉ ትሆን ዘንድ ለይቶ ያለሃጢያት የጠበቃትን ጉድፍ የሌለባትን የሰርግ ቤት አድፋ ነበር ማለት የሚቻለዉ ማን ነዉ፡፡ ከዘሯ የቀሩትን የእየሱስ ምስክርነት ያላቸዉን ሊዋጋ በባርህ አሽዋ ላይ ከቆመዉ በቀር ይቃወማት ዘንድ ማን ይደፍራል ? ለሁላችንም ማስተዋሉን አምላካችን ያድለን የዚህ ጽሁፍ መልእክት ድንግል ማርያምን ጥንተ አብሶ አላገኛትም የሚል ነው ፡፡ ምናልባት ይኸ መልስ በተለያየ ጊዜ የተነሱትን ጥያቄዎች ሁሉ ለመመለስ ይሞክራል ተብሎ ይገመታል፡፡ 1. አንዳንዶች፡- ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ የጠፋላት መልአኩ ባበሠራት ጊዜ ነው በማለት ይጽፋሉ፡፡ ይህ አባባል ከዚህ በፊት መልአክ ያበሠራቸው ማኑሄና ሚስቱ ፣ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ለምን ጥንተ አብሶ አልጠፋላቸውም ያሰኛል ? መሳ 13.2-3 ፣ ሉቃ 1.13 ፡፡ ጥንተ አብሶ የሚጠፋው በብሥራተ መልአክ ቢሆንማ ፣ አካላዊ ቃል ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ፣ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው በመሆን ፣ መከራ መቀበልና ፣ በመስቀል ላይ መሞት አያስፈልገውም ነበር ፡፡ በቀላሉ ውርደትንና ሞታችንን ሳይካፈል ፣ እልፍ አዕላፋት መላእክትን ልኮ ብሥራትን በመንገር ብቻ ጥንተ አብሶን ከሁላችንም ዘንድ ማጥፋት ይቀለው ነበር ፡፡ በሌላ በኩልም ፣ የቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ከጥንተ አብሶ ነጻ ማድረግ ከቻለ ፣ የአንድ መልአክን የብሥራት ቃል ከክርስቶስ ደምና ሞት ጋር እኩል አድርገነዋል ማለት ስለሚሆን ፈጽሞ የተሳሳተ መግለጫ ነው ፡፡ 2. አሁንም ሌሎች ደግሞ ጥንተ አብሶ የጠፋላት ፣ ጌታ በሚፀነሰበት ወቅት ፣ ከመቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ሲጸልላት ነው ይሉናል፡፡ ይህም ጌታ ሰው መሆን ያስፈለገውና ወደ እዚህ ምድር የመጣው አዳማዊውን በደል ማለትም ጥንተ አብሶን እንዴት አድርጐ ለማጥፋት ነው? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል ፡፡ መልሳችንም በመስቀል ላይ በሚፈጽመው ቤዛነትና በሚከፍለው መሥዋዕትነት ብቻ ነው የሚል ነው ፡፡ እንግዲህ እመቤታችን ጥንተ አብሶ ከነበረባት ፣ መድኃኒቴ ያለችውንም ቃል አጣምረን ደምረን ፣ እንደማናቸውም ሰው በመስቀል ላይ በሚፈጸም ቤዛነት ብቻ ከጥንተ አብሶ መዳን ነበረባት እንጂ ፣ አንዳንዶች እንደሚሉት መንፈስ ቅዱስ በጸለለባት ጊዜ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ንጽህና ከሌለ ደግሞ ጌታ የተጸነሰው ጥንተ አብሶ በነበራት አንዲት ሴት ማህጸን ነው ስለሚያሰኝ ፍጹም ስህተት ይሆናል(1) ፤ በመቀጠልም የዳዊት መዝሙርን እንደሚተረጉሙት ጌታችንንም በኃጢአት ተወለደ ሊያስብል ነውና(2) ፡፡ በሌላው ወገን ደግሞ መንፈስ ቅዱስም በበኩሉ ጥንተ አብሶን አንጽቶ ድህነትን የሚያስገኝ ከሆነ ፣ በዚህ ዓለም ላለነው የአዳም ልጆች ሁሉ ፣ ሁለተኛ አማራጭ የመዳኛ መንገድ አለን ብለን ልንመሰክር ነው ማለት ነው(3) ፤ ማለትም በኢየሱስ ሞትና ደም ሌላም በመንፈስ ቅዱስ መጽለል በኩል፡፡ ሎቱ ስብሐት !!! የፈሰሰውን ደም ፣ ስለ እኛ የተቀበለውን ፍዳና መከራ መካድና ተደራራቢ ስህተቶችን ማምጣት ፡፡ 3. ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ ወደ እመቤታችን በመጣ ጊዜ ፡- “ደስ ይበልሽ ፣ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው ፤ ከሴቶች መካከል አንቺ የተባረክሽ ነሽ ፡፡” በማለት አመስግኗታል (ሉቃ 1.28) ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ፣ ከእርሷ በፊት ይህን በሚመስል ምስጋና የተመሰገነ አንድም ፍጡር የለም ፡፡ ይኸ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእመቤታችን የተሰጠ ምስጋና ነው ፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር !!! እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጥንተ አብሶ ተይዛ ቢሆን ኖሮ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “ጸጋን የተመላሽ ሆይ” ሊላት አይችልም ነበር፡፡ ምክንያቱሳ ቢሉ ፣ ጥንተ አብሶ ጸጋዋን ጐደሎ ያደርግባት ነበርና ነው፡፡ አዳም በደልን እንደ ፈጸመ በቀጣዩ ያጋጠመው የመጀመሪያው ቅጣት ጸጋው መጉደሉ ወይም መገፈፉ ነው ፡፡ ይኸ የአዳም በደል አለባት ከተባለ ፣ ጸጋዋ እንደ ቀደም አባቷ መጉደል ይገባው ነበርና ፣ ታድያ መልአኩ እንዴትና ስለምን ኦ ምልአተ ጸጋ በማለት ሊያወድሳት ይችላል? 4. ሌሎች ደግሞ ሉቃ 1፡47 የተነገረውን ድንግል ማርያም በራሷ ላይ የምስክርነት ቃል እንደ ሰጠች አድርገው በማቅረብ ጥንተ አብሶ እንደነበረባት ለማስረዳት ይሞክራሉ ፡፡ ይኸን ቃል ለመናገር የሚገደደው ፍጡር የሆነ ሁሉ እንጅ አዳማዊ ኃጢአት ያለበት ብቻ እየተመረጠ አይደለም ፡፡ በአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አምሳል የተፈጠረ ፍጡር በሙሉ አምላኬ ፣ መድኃኒቴ ፣ በማለት አምላኩን ያወድሳል፡፡ ድንግል ማርያም በተለየ መድኃኒቴ የሚለውን የምስክርነት ቃል የሰጠችው ፣ ገና ኢየሱስ ሳይወለድና በመስቀል ላይ ሞቶ ሳያድናት ነው ፡፡ ሳይሞትና መስዋዕት ሳይሆን ደግሞ ስለድኀነት መናገር ስለማይቻል ፣ ከፍጥረት አስቀድማ ድና ነበር ያሰኘን እንደሁ እንጅ ፣ ገና ደሙን ያላፈሰሰና ያልሞተውን አምላኳንና ልጅዋን ፣ ሰው መሆኑን እንኳን አይታ ያላረጋገጠችውን የማህጸን የጽንስ ፍሬ መድኃኒቴ ብላለች በማለት ያልሆነ ትርጓሜም በመስጠት ወይም የትንቢት ቃል አስመስሎ መከራከር ፣ የሚያስኬድ ሆኖ አላየሁትም ፡፡ ከመስዋዕትነት በኋላ የተነገረ ቃል ቢሆን እንኳን ፣ ያንን ተንተርሶ ትንሽ ለማደናገር ክፍተት ይገኝ ነበር ፡፡ ቤዛነቱ ሳይፈጸም መድኃኒቴ ስላለች ፣ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በተለየ መንገድ ድናለች ወይም ቀድሞውንም ከጥንተ አብሶ ጠብቆ አቆይቷቷል ፣ ለማለት እንደፍራለን እንጅ አዳማዊ በደል አግኝቷታል የሚለው በየትም በኩል ማስማሚያ የለውም ፡፡ እግዚአብሔር ነቢይ ሊያደርግ የፈለገውን እንኳን “በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ” እያለ የተናገረ / ኤር 1፡5/ ፤ ለማደሪያውና እናት ትሆነው ዘንድ የመረጣትን ቅድስትና ብፅዕትማ ደግሞ ፣ ምን ያህል እንደ ሚጠበብላትና እንደ ሚያሰናዳት ባለ አእምሮ የሆነ ሰው ሁሉ ሊያጤነው ይገባል ፡፡ ከልማደ እንስትና ከሀልዮ (ሃሳብ) ፣ ከነቢብና (ንግግር) ፣ ከገቢር (ሥራ) ኃጢአት ነጻ ያደረጋት ፈጣሪ ጥንተ አብሶን አላስወገደላትም ማለት ፈጽሞ ቧልት ነው ፡፡ 5. ኢሳ 1፡9 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር የሚለውን ስለይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ህዝብ እንደተነገረ አድርገው የሚተረጉሙ አሉ ፡፡ ከቁጥር 9 ንባብ አስቀድሞ በቁጥር 8 ላይ ስለ ጽዮን ሴት ልጅ የሚናገረውንስ እነዴት መንደርና ከተማ አድርጐ መተርጐም ይቻላል ? ኢሳይያስ ነገሩን እያጠራልን ሲሄድ በምዕራፍ 2 ላይ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም እየተናገረ በቁጥር 2 ስለ ዘመን ፍጻሜ ክስተት ያወሳናል ፤ በቁጥር 3 ደግሞ ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል (አጽንኦት) ከኢየሩሳሌም ይወጣል ፤ ለአሕዛብ ሁሉ መንገዱን ያስተምራል ፣ በጎዳናውም እንደሚሄዱ ይናገራል ፡፡ እንዲያውም ዳግም አትታወሩ ብሎ ሊያሳርፈን ሲፈልግ ፣ አለፍ ብሎ በምዕራፍ 7፡14 ደግሞ ለዳዊት ቤት እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች ፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች ይልና ፣ ትንቢቱን ያስቀምጥልናል ፡፡ በመቀጠልም በምዕራፍ 9፡6 ደግሞ ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል በማለት የምትወልድውን ህፃን ማንነት በግልጽ ያበሥራል ፡፡ ስለዚህም መጽሐፉ የሚነግረን መንፈስ ቅዱስ በምዕራፍ 1፡9 ፤ 2፡2-3 ያስረዳውን ስውር ቃል በምዕራፍ 7፡14 ግልጽ እንደ አደረገለትና ፤ ይህንኑ የተስፋ ቃል ደግሞ በማቴዎስ 1፡18 በእውን እንደ ተረጐመው ነው፡፡ በመሆኑም ከመጀመሪያ ምዕራፍ አንስቶ በተደጋጋሚ በተለያየ ሥፍራ ስለ ድንግል ማርያም ተናግሯልና በኢሳ 1፡9 የተገለጸውም እሷን የሚመለከት ቃል ነው እንጅ ስለ አገርና ህዝብ የተነገረ አይደለም ፡፡ 6. ደግሞም ወንደ አላዉቅም አለች እንጂ ጥንተ አብሶ ስላለብኝ እንዴት ይሆንልኛል አላለችም፡፡ መልአኩም እንደምትጸንስ የልኡል እግዚብሄር ልጅ እግዚአብሄርን እንደምትወልድ እርሱም ታለቅ እንደሆን በዳዊት ዙፋ እንደሚቀመጥ ለመንግስቱም ፍጻሜ እንደሌለዉ ሲነግራት እንደሰዉ ልማድ ስለመሰላት ወንድ አላዉቅም አለችዉ በዚህም እንኳንስ በስጋዋ በሃሳቧም ንጽህት እንደሆነች እንረዳለን ባጠገቧ ያለዉን ዮሴፍን እንኳን አላሰበችምና፡፡ ከዚህ በኋላ ነዉ እንግዲህ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል የልዑል ሃይልም ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ካንቺ የሚወለደዉ ቅዱስ የእግዚበሄር ልጅ ይባላል ያላት ፡፡ ወንድ አላዉቅም ማለት ያለወንድ ዘር መዉለድ አይቻልም እኔ ደግሞ እንዲህ የማድረግ ሃሳብ ፈጽሞ የለኝም የሚል ትርጉም የሚሰጥ እንጂ ሃጢያተኛ ነኝ የሚል ትርጉም የለዉም፡፡ ለዚሀም ነዉ የምትወልደዉ ያለወንድ ዘር እንደሆነ ‹‹ መንፈስ ቅዱስ ባንችላይ የመጣል የልዑል ሃይልመ ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንች የሚወለደዉ ቅዱስ የእግዚብሄር ልጅ ይባላል ያላት፡፡ለመሆኑ መንፈስ ቅዱስ ስራዉ ማንጻት ብቻ ነዉ እንዴ ሃዋሪያት እኮ መንፈስን ቅዱስን እስክልክላችሁ ድረስ ከእየሩሳሌም እንዳትወጡ የተባሉት ቅዱሱ መንፈስ ካላጸናቸዉ በቀር የእዉነትን ቃል መሸከም ስለማይችሉ ነዉ፡፡ ማርያም ደግሞ ልትሸከም የተመረጠችዉ የቃሉን ባለቤት ነዉ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ያጸናጽ ዘንድ እንጅ ያነጻት ዘንድ እንዳልሆን እናስተዉል ፡፡ ደግሞም የልኡልም ሃይል ይጸልልሻል (ይጋርድሻል) በማለት የተጋረደች የንጉስ መንበር እንደምትሆን ነገራት እንጅ ፈጽሞ ስለ ሃሚያት መንጻት መልአኩ አልተናገረም፡፡ ለአባ ሕርያቆስ ፤ለቅዱስ ኤፍሬም ፤ለቅዱስ ያሬድ ፤ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተገለጸች ዕመቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት ትጎብኘን ፤ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን -አሜን ወስብሐት ለእግዚአብሔር —

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ